የአሜሪካ መንግስት መስሪያቤቶች የመዘጋት አደጋ አንዣቦባቸዋል
ሪፐብሊካኖች የመንግስት በጀት እንዲራዘም የቀረበውን ረቂቅ ባለማጽደቃቸው ነው በአስር አመት ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ የመንግስት መስሪያቤቶች ሊዘጉ ይችላሉ የተባለው
ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ ካልደረሱ 4 ሚሊየን የመንግስት ሰራተኞች አደጋ ላይ ይወድቃሉ ተብሏል
የአሜሪካ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የመዘጋት አደጋ አንዣቦባቸዋል ተባለ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጠናኛ አብላጫ ያላቸው ሪፐብሊካኖች (221 ለ212) የመንግስትን በጀት ለማራዘም በራሳቸው ፓርቲ የቀረበውን ረቂቅ ማጽደቅ ባለመቻላቸው ነው የመንግስት መስሪያ ቤቶቹ ሊዘጉ ይችላሉ የተባለው።
የሀገሪቱን መንግስት በጀት በ30 ቀናት ለማራዘምና የመንግስት መዘጋቱን ለማስቆም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ 232 ለ 198 በሆነ ድምጽ ውድቅ ተደርጓል።
ይህም 4 ሚሊየን የአሜሪካ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ እንዲቋረጥ እና በርካታ ተቋማትም በከፊል እንዲዘጉ የሚያደርግ ነው ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ሁለቱ ፓርቲዎች እስከ ነገ ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉም በአስር አመት ውስጥ አራተኛው የመንግስት መዘጋት አይቀሬ ይሆናል።
የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬቪን ማካርቲ የበጀት ማራዘሚያው ዛሬ ወይንም ነገ እንደሚጸድቅ ያምናሉ።
ሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ከስምምነት ደርሰው የበጀት ማራዘሚያው የማይጸድቅ ከሆነ ግን የአሜሪካ ኢኮኖሚ ክፉኛ እንደሚጎዳ የሀገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር ጃኔት የለን ተናግረዋል።
ከአራት ወራት በፊትም 31 ትሪሊየን ከደረሰው የሀገሪቱ እዳ ጋር በተያያዘ በዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነት የመንግስት መስሪያቤቶች በከፊል እንዲዘጉ ማድረጉ አይዘነጋም።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የበጀት ማራዘሚያው አለመጽደቁ የሀገሪቱን መከላከያ ሃይል እንደሚጎዳ በመግለጽ የመንግስት መዘጋትን መፍቀድ የለብንም ሲሉ ተደምጠዋል።
አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገው ድጋፍ እና የስደተኞች ጉዳይ በበጀቱ ላይ ዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖችን ለሁለት ከፍሏል።
ፓርቲዎቹ ዛሬ ወይም ነገ ከስምምነት ላይ ካልደረሱም የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ፓርኮች፣ አየር መንገዶች እና ሌሎች ግዙፍ ተቋማት ከበጀት ውጭ ሆነው ስራቸው ክፉኛ ይስተጓጎላል ተብሏል።