የእስራኤል ጦር በበኩሉ መርከቦቹ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት የላቸውም ብሏል
የአሜሪካ የጦር መርከብ በቀይ ባህር ሶስት የሃውቲ ታጣቂዎች ድሮኖችን መትታ መጣሏ ተገለጸ።
ብሪታንያን ጨምሮ ከ14 ሀገራት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሶስት የንግድ መርከቦች ከየመን የሃውቲ ታጣቂዎች የጥቃት ኢላማ በመሆናቸው ነው የአሜሪካ ጦር መርከብ ድሮኖቹን የመታችው።
ሁለት መርከቦች በሚሳኤል መመታታቸው የተገለጸ ሲሆን የደረሰው ጉዳት ግን አልተብራራም።
የብሪታንያ ማሪታይም ኤጀንሲ ትናንት ማምሻውን የንግድ መርከቦች በባብ አል ማንደብ አካባቢ በድሮን ስለመመታታቸው መግለጹ የሚታወስ ነው።
የሃውቲ ታጣቂ ቡድን ቃል አቀባይ የቡድኑ ባህር ሃይል በሁለት የእስራኤል መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሱን መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ መርከቦቹ ከእስራኤል ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም የሚል መግለጫ አውጥቷል።
በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካን ተልዕኮ የሚያስፈጽመው “ሴንትኮም” እንዳስታወቀው የባሃማስ እና ፓናማ ሰንደቅ አላማ የሚያውለበልቡት መርከቦች በብሪታንያና ሊሎች ሀገራት የሚተዳደሩ ናቸው።
የድሮን ጥቃት ሙከራው የተለያዩ ሀገራት መርከበኞችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤ የአለማቀፉን የንግድ ስርአትም ያዛባል ያለው ሴንትኮም፥ ኢራን የጥቃቱ ዋነኛ ጠንሳሽ ናት ሲልም ወቅሷል።
ዋሽንግተን ከአጋሮቿ ጋር በመሆንም በቴህራን እና በምታስታጥቀው ሃውቲ ላይ እርምጃ እንደምትወስድ ዝቷል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የሃውቲ ታጣቂዎች ከፍልስጤሙ ሃማስ ጎን መሰለፋቸውን ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን በመተኮስ አሳይተዋል።
ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች በቀይ ባህር ዝር እንዳይሉ ከማሳሰብም አልፈው በእስራኤላዊ ባለሃብት የሚተዳደር ኩባንያ መርከብን ማገታቸው አይዘነጋም።