የአሜሪካ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶስት ሀገራት ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
የዋሸንግተን ባለስልጣናት በኢትዮጵያ አንጎላ እና ካሜሩን ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል
ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት የአሜሪካ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ አመራሮች ጋር የመገናኘት እቅድ እንደሌላቸው ተገልጿል
የአሜሪካ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶስት ሀገራት ጉብኝት ሊያደርጉ ነው፡፡
የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ሪቻርድ ቬርማ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን እንደሚጎበኙ ተገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ በድረገጹ ባወጣው መግለጫ በምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቬርማ የተመራ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ፣ ካሜሩን እና አንጎላ ጉብኝት ያደርጋል፡፡
ወደ አዲ አበባ የሚመጣው የአሜሪካ ልዑክ ከአፍሪካ ህብረት አመራሮች ጋር እንደሚመክር የተገለጸ ሲሆን ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር የመወያየት እቅድ ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም፡፡
ሪቻርድ ቨርማ ወደ ካሜሩን አቅንተው በሚያደርጉት ጉብኘት በሁለትዮሽ የጤና፣ ሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ከያውንዴ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በአንጎላው ጉብኝት ላይ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ወይም ዩኤኤይድ ሃላፊ ሳማንታ ፓወር ጋር አብረው እንደሚጓዙም ተገልጿል፡፡
በሉዋንዳ በሚካሄደው የአሜሪካ እና አንጎላ መሪዎች ውይይት የንግድ፣ ግብርና፣ ጤና እና ማህበረሰብ መሪዎች ይሳተፋሉም ተብሏል፡፡
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ላሉት ጦርነቶች ለምን ትኩረት ነፈጉ?
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በጣልያኗ ካፕሪ እየተካሄደ ባለው የቡድን ሰባት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መድረክ ላይ እየተሳተፉ ናቸው፡፡
ሚኒስትሮቹ ባወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ወንጀለኞች እንዲጠየቁ፣ የሽግግር ፍትህ እንዲሰፍን እና የፖለቲካ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ያሳሰበው መግለጫው ከሶማሊያ ጋር ያለው መካረርም በዲፕሎማሲ መንገድ እንዲፈቱም ጥሪ አቅርቧል፡፡