የአሜሪካ እርዳታ ካልደረሰ የዩክሬን ጦር ለማፈግፈግ እንደሚገደድ ዘለንስኪ ተናገሩ
የሩሲያ ኃይሎች ባለፈው ወር በምስራቅ ዩክሬን የምትገኘውን አቭዲቪካን ጨምሮ በርካታ መንደሮችን ተቆጣጥረዋል
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ዩክሬን አሜሪካ ቃል የገባችላትን ወታደራዊ እርዳታ የማታገኝ ከሆነ ጦሯ የተወሰነ ደረጃ ወደ ኋላ ሊያፈገፍግ እንደሚችል ተናግረዋል
የአሜሪካ የጦር መሳሪያ እርዳታ ካልደረሰ የዩክሬን ጦር ለማፈግፈግ እንደሚገደድ ዘለንስኪ ተናገሩ።
ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ለዋሽንግተን ፖስት በሰጡት ቃለምልልስ ዩክሬን አሜሪካ ቃል የገባችላትን ወታደራዊ እርዳታ የማታገኝ ከሆነ ጦሯ የተወሰነ ደረጃ ወደ ኋላ ሊያፈገፍግ እንደሚችል ተናግረዋል።
ዘለንስኪ "የአሜሪካ ድጋፍ የለም ማለት የአየር መከላከያ ሰርአት የለንም፣ ፓትሪዮት ሚሳይል እና ለኤሌክትሮኒክ ዋርፌር የሚሆን ጃመር የለንም ማለት ነው" ብለዋል
ከዚህ በተጨማሪ እርዳታውን የማናገኝ ከሆነ "ደረጃ በደረጃ ወደ ኋላ ለማፈግፈግ እንገደዳለን። ወደ ኋላ ለላማፈግፈግ አማራጭ እየፈለግን ነው" ሲሉ ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ የጦር መሳሪያ የሚያጥረን ከሆነ የግንባር ይዞታዎችን ማሳጠር እና ማፈግፈግ ሊኖርብን ይችላል ብለዋል።
የዲሞክራቱ ፕሬዝደንት ባይደን በሪፐብሊካን ቁጥጥር ስር ያለው የተወካዮች ምክርቤት የዩክሬንን የወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያጸድቀው ቢጠይቁም፣ የምክርቤቱ አፈጉባኤ ማይክ ጆንሰን ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች አሉ በማለት ጉዳዩን ለወራት ይዘውታል።
ዘለንስኪ ለጆንሰን ስልክ በመደወል የእርዳታው መጽደቅ ለዩክሬን በጣም አስፈላጊ ነው ሲሉ ነግረዋቸዋል።
የሩሲያ ኃይሎች ባለፈው ወር በምስራቅ ዩክሬን የምትገኘውን ጰ አቭዲቪካን ጨምሮ በርካታ መንደሮችን ተቆጣጥረዋል
ዩክሬን ከተማዋን እና መንደሮቹን ለቃ ለውጣት የተገደደችው የምዕራባውያን እርዳታ በፍጥነት ባለመድረሱ ምክንያት የተተኳሽ እጥረት ያጋጠማቸው ወታደሮች ከበባ እንዳይፈጸምባቸው ነው ማለቷ ይታወሳል።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ በዚህ ቃለ ምልልሳቸው ዩክሬን ያጋጠማትን የሚሳይል እጥረት ለመቅረፍ በሀገር ውስጥ መሳሪያ እያመረተች እና የአየር መከላከያ ስርአት እየገነባች ቢሆንም "በቂ አይደለም"ብለዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ሁለት አመት ያስቆጠረ ሲሆን ሩሲያ በዩክሬን በኃይል እና በሌሎች ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ላይ እያደረገች ያለውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።
ዩክሬንም በሩሲያ ውስጥ ዘልቃ በመግባት በሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያዎች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን መግለጿ ይታወሳል።