ቻይና አፈ ጉባኤዋ ታይዋንን ከጎበኙ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ማስጠንቀቋ ይታወሳል
የአሜሪካ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የእስያ ጉዟቸውን ጀመሩ።
የአሜሪካ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ከዛሬ ጀምሮ ታይዋንን እና ሌሎች የእስያ ሀገራትን እንደሚጎበኙ መግለጻቸው ይታወሳል ።
የአፈ ጉባኤውን የታይዋን ጉብኝት ተከትሎም ቻይና ወታደራዊ እርምጃዎችን ጨምሮ ማንኛውንም አይነት እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ማስጠንቀቋ አይዘነጋም።
በዚህም መሰረት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የእስያ ጉብኝታቸውን የጀመሩ ሲሆን ለሩቅ ምስራቅ ሀገራት ቀረብ ወደምትለው የአሜሪካዋ ሀዋይ ደሴት መብረራቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ፔሎሲ በጉብኝታቸው ታይዋን ተካታ የነበረች ሲሆን ይህ የአፈጉባኤዋ የጉብኝት እቅድ ማስተካከያ ሳይደረግበት እንዳልቀረ ሲኤንኤን የቅርብ አጋራቸውን ጠቅሶ ዘግቧል።
የአፈጉባኤዋ የታይዋን ጉብኝት የተሰረዘው የቻይናን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ እንደሆነም ተጠቅሷል።
በዚህም ምክንያት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የእስያ ጉብኝታቸው ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ማሌዢያ፣እና ሲንጋፖር እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።
አሜሪካ እና ቻይና በታይዋን ጉዳይ ከፍተኛ ያለመግባባት ችግር ውስጥ ሲሆኑ፤ አሜሪካ ታይዋን የቻይና አካል አይደለችም ስትል ቻይና በበኩሏ ታይዋን የግዛቴ አንድ አካል ናት የሚል ዕምነት አላት።
የሁለቱ ሀገራት ፕሬዝዳንቶች በትናንትናው ዕለት በስልክ የተወያዩ ሲሆን ውይይቱ ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካዋ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ቻይና የግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥራትን ታይዋንን ለመጎብኘት ማቀዳቸው ሁለቱን ሀገራት ከፍተኛ አለመግባባት ውስጥ ከቷቸዋል።