አሜሪካ በዚምባቡዌ ፕሬዝደንት ላይ ማዕቀብ ጣለች
የአሜሪካ ምክትል የገንዘብ ሚኒስትር ዋሊ አዲየሞ "ማዕቀቦቻችን የዚምባቡዌ ህዝብን የመጉዳት አላማ የላቸው" ብለዋል
ምናንጋግዋ ከቀድሞ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ ቀጥሎ በተከታታይ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሁለተኛው መሪ ሆነዋል
አሜሪካ በዚምባቡዌ ፕሬዝደንት ላይ ማዕቀብ ጣለች።
አሜሪካ በመብት ጥሰት ተሳትፈዋል ባለቻቸው የዚምባቡዌ ፕሬዝደንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ላይ ማዕቀብ መጣሏ ተገልጿል።
ፕሬዝደንቱ እና ባለስልጣናቱ በአሜሪካ ሀገር ያለ ንብረት እንዳያንቀሳቅሱ እና ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርገው ይህ ማዕቀብ ለሁለት አስርት አመታት ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ የሚተካ መሆኑን ቪኦኤ ዘግቧል።
የአሜሪካ ምክትል የገንዘብ ሚኒስትር ዋሊ አዲየሞ "ማዕቀቦቻችን የዚምባቡዌ ህዝብን የመጉዳት አላማ የላቸው" ብለዋል።
"ማዕቀባችን በውስን ኢላማዎችን ላይ እንዲያተኩር አድርገናል። የፕሬዝደንት ምናንጋግዋ የወንጀለኛ ባለስልጣናት እና ነጋዴዎች ትስስር በዚምባቡዌ ህዝብ ላይ ለሚፈጸመው የመብት ጥሰት እና ሙስና በዋናነት ተጠያቂ ናቸው" ብለዋል ምክትል ገንዘብ ሚኒስትሩ።
በዚምባቡዌ እየተፈጸመ ያለው ሙስና እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚያሳስባቸው የገለጹት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አዲሱ እርምጃ እየተወሰደ ያለው ጠንካራ የፖሊሲ ማዕቀብ አካል ነው ብለዋል።
"የዚምባቡዌ መንግስት አባላትን ጨምሮ ቁልፍ ባለስልጣናት ለተፈጸመው የመንግስት ሀብት ዝርፊያ ኃላፊነት ይወስዳሉ" ሲሉ ብሊንከን ተናግረዋል።
ምናንጋግዋ ባለፈው ነሐሴ በተካሄደው እና አለምአቀፍ ተቋማት የዲሞክራሲ መመዘኛዎችን አያሟላም ባሉት ምርጫ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን መመረጣቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ምናንጋግዋ ከቀድሞ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ ቀጥሎ በተከታታይ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሁለተኛው መሪ ሆነዋል።
ፕሬዝደንት ባይደን በትናንትናው እለት በቀድሞ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደዝሊው ቡሽ በ2003 ተጥሎ የነበረው የማዕቀብ ፕሮግራም ማብቃቱን ይፋ አድርገዋል።