አሜሪካ በመንግስት ተቋማት ቲክቶክ መጠቀምን ልታግድ ነው
ቻይና በአሜሪካ ከ130 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚ ያለውን ቲክቶክ ለስለላ ልትጠቀምበት ትችላለች በሚል ነው እገዳውን የምትጥለው
ቲክቶክ ግን እርምጃው ከደህንነት ጋር የሚያያዝ ሳይሆን ፖለቲካዊ ፍላጎት የተጫነው ነው በማለት ተቃውሞታል
አሜሪካ የመንግስት ሰራተኞች በመንግስት ኮምፒውተሮችና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ቲክቶክ እንዳይጠቀሙ ልታግድ መሆኑ ተነግሯል።
ቻይና በአሜሪካ ከ130 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚ ያለውን ቲክቶክ ለስለላ ልትጠቀምበት ትችላለች የሚል ስጋት ነው እገዳውን ሊያስጥል የተቃረበው።
የሀገሪቱ ህግ አውጪዎች ያረቀቁት ረቂቅ ምክረ ሃሳብም ባለፈው ሳምንት በሴኔቱ ተቀባይነት በማግኘቱ ህግ ሆኖ ሊጸድቅ ነው።በቀጣዩ ሳምንትም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፊርማቸውን አኑረውበት ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
ህጉ በጸደቀ በ60 ቀናት ውስጥ በየትኛውም የአሜሪካ የፌደራል ተቋም የኮምፒውተር ስርአት ውስጥ ቲክቶክን የማስወገድ ስራው እንደሚጀመርም ነው የተነገረው።
አሜሪካ ተቀባይነቱ እየጨመረ የሄደውን ቲክቶክ አንዱ የብሄራዊ ደህንነት ስጋቷ አድርጋ መመልከት ከጀመረች ሰነባብታለች።
የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ ዳይሬክተር ክርስቶፈር ራይ የቻይና መንግስት መተግበሪያውን በመጠቀም ደንበኞቹን እየሰለለ ነው፤ ይህም የብሄራዊ ደህንነታችን ስጋት ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ዋይትሃውስ፣ የመከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በመንግስት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ቲክቶክን መጠቀም ማገዳቸው የሚታወስ ነው።
ከትናንት በስቲያም የሉዚያና እና ዌስት ቨርጂኒያ ግዛቶች ተመሳሳይ ወሳኔ ማሳለፋቸውም ተዘግቧል።
ከ50ዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች 19ኙ በከፊልም ቢሆን ቲክቶክን በመንግስት ተቋማት መጠቀም ከልክለዋል ነው የተባለው።
አዲሱ ረቂቅ ህግ ከ130 ሚሊየን የቲክቶክ ተጠቃሚ አሜሪካውያን ውስጥ 4 ሚሊየን ገደማውን ብቻ የሚያካትት ነው ቢባልም የኩባንያውን ተቀባይነት እንደሚሸረሽረው ባለሙያዎች መናገራቸውን ሬውተርስ አስነብቧል።