አቶ ጌታቸው ረዳ “የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ጠላቶች ግጭት ለመፍጠር እየጣሩ ነው” አሉ
በደቡብ ትግራይ እየታየ ያለው ክስተት ከፌደራል ወይም ከአማራ ክልል ጋር የተፈጠረ ግጭት አይደለም ብለዋል
በትግራይ ደቡባዊ ዞንና በአማራ ክልል ጋር አዋሳኝ አካባቢዎች ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ ግጭት መከሰታቸው ተነግሯል
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ “የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ጠላት የሆኑ ሃይሎች ግጭት ለመፍጠር እየጣሩ ነው” ሲሉ ከሰሱ።
በትግራይ ደቡባዊ ዞንና በአማራ ክልል ጋር አዋሳኝ አካባቢዎች ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት መከሰታቸው ተነግሯል።
ይህንን ተከትሎም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በስተላለፉት መልእክት፤ “በደቡብ ትግራይና በሌሎች በኃይል በተያዙ የትግራይ ግዛቶች እየታየ ያለው ክስተት በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር፤ በህወሓት ወይም ደግሞ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት አይደለም” ብለዋል።
ግጭቱ የፈጠሩት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ጠላት የሆኑ ኃይሎች ናቸው” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት ጠላቶች የሚሏቸውን በስም አልጠቀሱም።
ግጭቱን የቀሰቀሱ አካላትም “የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እየተደረገ ያለውን መልካም ግንኙነት ለማደናቀፍ ያለሙ” እንደሆነም አስታውቀዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ አክለውም፤ ችግሮችን ለመፍታት እና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ሁለቱ ወገኖች በአዲስ አበባ እየመከሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በትግራይ ደቡባዊ ዞንና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተቀሰቀሰ የተባለዉን ግጭት ተከትሎ የአማራ ክልል መንግሥት እስካሁን ያለዉ ነገር የለም።
በትግራይ ደቡባዊ ዞንና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት መከሰታቸው ከስፍራው የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህንን ተከትሎም ግጭቱን በመስጋት በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ከአላማጣ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየሸሹ መሆናቸዉ ተመልክቷል።
የአማራ ክልል መንግስት ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ ነዋሪዎችን በመግደልና በማሰቃየት ላይ ይገኛል” ሲል መክሰሱ ይታወሳል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ቀደም ብሎ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው አማራ ክልል መንግስት “የትግራይ መሬቶችን የግዛቱ አካል በማድረግ” በክልሉ ካርታ ላይ አስፍሯ” በማለት መክሰሱ አይዘነጋም።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ የአማራ ክልል በመማሪያ መጽሐፍት ላይ ያወጣው የተሳሳተ ካርታ ላይ በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ በመግለጫው አስተጠንቅቆ ነበር።
ይህ የማይሆን ከሆነ ግን “ይህን ተከትሎ ለሚመጣው ነገር ሁሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው የአማራ ክልል መሆኑን ልናሳውቅ እንወዳለን” ብሏል።
የፌደራል መንግስት የሁለቱ ክልሎችን መግለጫ ተከተሎ በሰጠው ምለሽም፤ “በትግራይ ክልል በኩል በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ የሚታየው አዝማሚያ ተገቢነት የሌላውና የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ነው” ማለቱ ይታወሳል።
የወሰንና የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳይ እልባት እስከሚያገኝ ድረስ የፌደራል መንግስት የመከላከያ ሰራዊትን በማሰማራት የአካባቢውን ደህንነት የማስከበርና የመቆጣጠር ስራ እንደሚሰራ መግለጹም ይታወሳል።