ከአላማጣና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ ማለፉን ተመድ አስታወቀ
በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ባገረሸው ግጭት ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን አስታውቋል
ተፈናቃዮቹ ሰሜን ወሎ ቆቦ እና ዋግህምራ ሰቆጣ ከተሞች መጠለላቸው ተመድ ተገልጿል
በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ባገረሸው ግጭት ከአላማጣና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ ማለፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።
እንደ ድርጅቱ ሪፖርት ከሆነ ከሰሞኑ በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ በሆኑን አላማጣ ከተማ እና ራያ አላማጣ፣ ዛታ እንዲሁም ኦፍላ ወረዳዎች ባገረሸው ግጭት ምክንያት ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።
በከተሞቹ ሚያዚያ 5 እና 6 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ በላይ መድረሱን ነው ተመድ ያስታወቀው።
ከተፈናቃዮቹ መካከልም 40 ሺህ ሰዎች በሰሜን ወሎ ቆቦ እንዲሁም 8 ሺህ 300 ሰዎች ገድሞ ዋግህምራ ዞን ሰቆጠ ከተማ መጠለላቸውን ተመድ የዞኖቹን አስተዳደሮች ዋቢ አድርጎ በሪፖርአቱ አመላክቷል።
ተመድ አክሎም ተፈናቃዮች በአብዛኛው ሴቶች፣ ህጻናት፣ ታዳጊዎች እና አረጋውያንን ናቸው ያለ ሲሆን፤ ከእነዚህም አብዘኞቹ በማኅበረሰቡ ባሉ ቤቶች ለመጠለል እየሞከሩ እንደሆነ እና ሌሎች ደግሞ ከቆቦ ከተማ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኝ ጋራ ሌንጫ በተሰኘው የኢንዱስትሪ መንደር ክፍት ቦታ ላይ ተጠልለው ይገኛሉ ብሏል።
በኢነዚህ አካባቢዎች ተጠለሉ ሰዎች ለበልግ ዝናብ መጋለጣቸውን ተከትሎም የተወሰኑትን ተፈናቃዮች ወደ ተሸለ ስፍራ የማዘዋወር ስራ እየተሰራ እንደሆነም ነው ተመድ ያስታወቀው።
በአካባቢው የፌደራል የጸጥታ ኃሎች ጣልቃ መግባታቸውን ተከትሎም ከትናንት ሚያዝያ 14 2016 ዓ.ም ጀምሮ በአላማጣ፣ ቆቦ እና በወልዲያ ከተሞች ያለው ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑንም ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያስታወቀው።
ከአላማጣ ወደ ቆቦ የሚወስደው እንዲሁም ከአላማጣ ወደ ማይጨው የሚወስዱ መንገዶች ለትራንስፖርት ክፍት መሆናቸውን እንዲሁም ባንክን የመሳሰሉ ሕዝባዊ አገልግሎቶች ስራ መጀመራቸውንም ተመድ በሪፖርቱ አመላክቷል።
በአሁኑ ወቅትም መንግስት እና የሰብአዊ አጋሮች ግጭቱን ተከትሎ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ መስጠት መጀመራቸውንም ነው ተመድ በሪፖርቱ ያስታወቀው።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ ክልል ያለው የሀገር መከላከያ ሰሜን እዝ በታጣቂዎች መጠቃቱን ተከትሎ ነበር የተከሰተው፡፡
ለሁለት ዓመት የዘለቀው ይህ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ የቆመ ቢሆንም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ መተግበር አልቻለም፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የትግራይ እና አማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው የራያ አካባቢ ዳግም ግጭት ተከስቷል፡፡
ግጭቱ የተከሰተው የህወሃት ታጣቂዎች ወደ አካባቢዎቹ በመምጣታቸው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ነዋሪዎችም ለደህንነታቸው በመስጋት ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡
በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተቀሰቀሰ የተባለዉን ግጭት ተከትሎ የአማራ ክልል መንግሥት ህወሃት ለአራተኛ ጊዜ ወረራ ፈጽሞብኛል ብሏል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው “በደቡብ ትግራይና በሌሎች በኃይል በተያዙ የትግራይ ግዛቶች እየታየ ያለው ክስተት በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር፤ በህወሓት ወይም ደግሞ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት አይደለም” ብለዋል።