የከብቶችን ህዋሳት በመውሰድ በቤተሙከራ የሚበለጽገው ስጋ ጣዕሙ እንደ ዶሮ ስጋ ተወዳጅ ነው ተብሎለታል
አሜሪካ በቤተሙከራ የተሰራ ስጋ ለገበያ እንዲቀርብ ፈቃድ መሰጠቷ ተገለፀ።
ኦፕሳይድ ፉድስ እና ጉድ ሚት የተባሉ ሁለት የአሜሪካ ኩባያዎች በቤተሙከራ የተሰራ ስጋን እንዲሸጡ በትነትናው እለት ከአሜሪካ ግብርና ሚኒስቴር ፈቀድ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
ለሁለቱ ኩባንያዎች የተሰጠው ፈቃድም በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በቤተሙከራ የተሰራ ስጋ የምርት ሽያጭ መንገድ መክፈቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ድርጅቶቹ ከእንስሳት ህዋሶች ናሙና የተገኘ በመጠቀም በቤተ ሙከራ ውስጥ የተሰራው ምርት “ስጋ” ተብሎ እንዲመዘገብ ባለብዙ ደረጃ የማፅደቅ ሂደት በማጠናቀቅ ቀዳሚ ናቸው ተብሏል።
አሜሪካ በቤተ ሙከራ ለተሰራው ስጋ ፈቃድ መስጠቷን ተከትሎ በላብራቶሪ የተመረተ ስጋን በመሸጥ ከሲንጋፖር በመቀጠል ሁለተኛዋ ሀገር ሆናለች።
ሲንጋፖር በሳይንሳዊ ሂደት የሚገኘውን ስጋ ጥቅማ ላይ እንዲውል በመወሰን ቀዳሚዋ ሀገር ናት።
በሳይንሳዊ ሂደት የሚመረተው ስጋ ጤናማነትም በአሜሪካ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ተረጋግጦ የሰው ልጆች ይመገቡት ዘንድ ቀደም ብሎ ፈቃድ መስጠቱ ይታወሳል።
አፕሳይድ ፉድስ በያዝነው የፈረንጆቹ አመት በተለያዩ የአሜሪካ ምግብ ቤቶች የቤተሙከራውን ስጋ ለገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።
ኩባንያው ምርቱን በእያንዳንዱ የመሸጫ መደብሮች ውስጥ ለማቅረብም አምስት አመታትን ጠብቁኝ ማለቱን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
አፕሳይድ አሁን ባለው አቅም በአመት 400 ሺህ ፓውንድ የሚመዝን ስጋን ነው ማቅረብ የሚችለው።
ይህም ከ106 ሚሊየን ፓውንድ በላይ የስጋ ፍላጎት ላላት አሜሪካ ከቁጥር የሚገባ ባይሆንም፥ ኩባንያው በየአመቱ የሚያደርጋቸው ማስፋፊያዎች የተወሰነ ቢሆንም ክፍተትን እንደሚሞላ ይጠበቃል።
ሌላኛው ተቀማጭነቱን ካሊፎርኒያ ያደረገ “ጎድ ሚት” የተሰኘ ተቋምም እንደ አፕሳይድ ፉድስ ሁሉ የቤተሙከራ ስጋውን ለማቅረብ የአሜሪካ የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንን ፈቃድ እየተጠባበቀ ነው ተብሏል።