አሜሪካ ለኮፕ28 ጉባኤ ግዙፍ ልኡክ እንደምትልክ ተገለጸ
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀጠናዊ ጉዳዮች ቃል አቀባዩ ሳም ዋርበርግ በጉባኤው ዙሪያ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ አድርገዋል
ቃል አቀባዩ አረብ ኤምሬትስ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን በመዋጋት ረገድ የአሜሪካ ሁነኛ አጋር ናት ብለዋል
አሜሪካ በአረብ ኤምሬትስ በሚካሄደው የአለማቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ28) በታሪኳ ግዙፉን ልኡክ ለማሳተፍ ዝግጅት እያደረገች ነው።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀጠናዊ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ሳም ዋርበርግ በኒውዮርክ ከተሄደው የአየር ንብረት ተስፋ ጉባኤ ጎን ለጎን ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ቃል አቀባዩ በዱባይ በሚካሄደው ጉባኤ ለመሳተፍ በርካታ ሚኒስትሮች እና የስራ ሃላፊዎች እያነጋገሯቸው መሆኑንና በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛው ልኡክ በጉባኤው ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
“አረብ ኤምሬትስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እየወሰደች ነው” ያሉት ዋርበርግ፥ ኤምሬትስ ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ ከአሜሪካ ጋር በአጋርነት እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።
ኤምሬትስ የኮፕ28 ጉባኤን ከማዘጋጀቷ በፊት ያከናወነቻቸውን የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል ትብብርን ማስቀደሟንም አድንቀዋል።
“እንደ ማስዳር ባሉ ኩባንያዎች በሶላርና ሌሎች ታዳሽ ፕሮጀክቶች የተገኙ አመርቂ ውጤቶች ኤምሬትስ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት ያሳያል”ም ነው ያሉት።
አረብ ኤምሬትስ የኮፕ28 ጉባኤን የተሳካ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኑንም ነው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀጠናዊ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ሳም ዋርበርግ ለአል ዐይን የተናገሩት።
ዋርበርግ በግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ኢራቅ፣ ታይላንድ እና ኩዌት የሰሩና አረብኛ ከሚናገሩ የአሜሪካ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ናቸው።
በዋሽንግተን በሚገኘው የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መስራታቸውም ቀጠናውን በደንብ እንዲረዱት አድርጓቸዋል።