አሜሪካ ከ15 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሞት ፍርደኛን በጥይት ደብድባ ልትገድል ነው
ግለሰቡ ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ ልዩ ጥይት በሶስት የፖሊስ አባላት በተመሳሳይ ሰአት ተተኩሶበት ቅጣቱ እንደሚፈጸምበት ታውቋል

የደቡብ ካሮላይና ነዋሪው የሞት ቅጣቱ የተላለፈበት የቀድሞ ፍቅረኛውን ወላጆች በቤዝቦል ዱላ ደብድቦ በመግደል ነው
የቀድሞው ፍቅረኛውን ወላጆች በቤዝቦል ዱላ ደብድቦ የገደለው የደቡብ ካሮላይና ነዋሪ ከ15 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥይት እንዲገደል ተወሰነ፡፡
ብራድ ሲግመን የተባለው የ67 አመት አዛውንት በፈረንጆቹ 2001 ዴቪድ እና ግላዲ ላርክ የተባሉ የፍቅረኛው ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት በማቅናት በአሰቃቂ ድብደባ ህይወታቸው እንዲያልፍ በማድረግ በቁጥጥር ስር ውሎ ቆይቷል፡፡
የግለሰቡ ጠበቆች እንዳሉት በአሜሪካ ለ15 አመታት ተፈጽሞ የማያውቀው የሞት ፍርደኛን የመቅጫ መንገድ ድጋሚ ስራ ላይ ሊውል የቻለው በእስረኛው ጥያቄ መሰረት ነው፡፡
በኤሌክትሪክ ወንበር እና በገዳይ መርፌ ተወግቶ መሞት አማራጭ የቀረበለት ብራድ በሁለቱ መንገዶች ፈጣን ውጤታማነት ላይ ጥርጣሬ ስላደረበት በጥይት ተደብድቦ መሞትን መርጧል፡፡
የብራድ ሲግመን የሞት ቅጣት በዛሬው ዕለት በመረጠው መንገድ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከመጋረጃ ጀርባ የቆሙ ሶስት የፖሊስ አባላት በልዩ ሁኔታ በተዘጋጁ ጥይቶች ደረቱ ላይ በተመሳሳይ ጊዜ ጠመንጃዎችን በመተኮስ ቅጣቱን የሚያስፈጽሙ ይሆናል፡፡
ፖሊሶቹ በልዩነት የተዘጋጁ ጥይቶችን የሚተኩሱት ከ4.6 ሜትር ርቀት ላይ ሆነው ነው፤ ቀጥሎም ሀኪሞች የግለሰቡን ሞት አረጋግጠው ቅጣቱ ይጠናቀቃል፡፡
በግዛቱ ህግ መሰረት ተቀጪው ግለሰብ ወደ መገደያ ክፍሉ ሲገባ ፊቱ በጭንብል ተሸፍኖ ሰውነቱ በወንበር ላይ ታስሮ በደረቱ ላይ የኢላማ ምልክቶች እንዲቀረጹበት ያዛል፡፡
አሜሪካ በ1976 የሞት ቅጣትን ድጋሚ ካሻሻለችበት ጊዜ ጀምሮ ማንም የደቡብ ካሮላይና ገዥ ለሞት ፍርደኛ ምህረት አድርጎ አያውቅም፡፡
ይህ የሞት ቅጣቱ ሲፈጸም ግለሰቡ እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ በአሜሪካ በጥይት የተገደለ የመጀመሪያው ሰው የሚሆን ሲሆን ሀገሪቱ በ1976 የሞት ቅጣት ህግን እንደገና ካወጣች በኋላ ደግሞ አራተኛው ሰው ይሆናል።
የደቡብ ካሮላይና ግዛት የገዳይ መርፌዎች አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ በ2022 ነበር 54 ሺህ ዶላር ወጪ በማድረግ ሰዎች በጥይት ተደብድበው የሚገደሉበትን ስፍራ ያዘጋጀችው፡፡
በግዛቱ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው አብዛኞቹ እስረኞች በኤሌክትሪክ የሚገደሉ ሲሆን ነገር ግን ሶስቱ የቅርብ ጊዜ ግድያዎች በገዳይ መርፌ የተደረጉ ናቸው፡፡
በመላው አሜሪካ ከ1976 ወዲህ በጥይት ተደብድበው የተገደሉ እስረኞች አጠቃላይ ቁጥር 3 ብቻ ነው፡፡