አሜሪካ እርዳታውን ለቁልፍ ሀገራት የምትሰጠው ለራሷ ጥቅም እና ለዓለም መረጋጋት እንደሆነ ትገልጻለች
የአሜሪካንን ወታደራዊ እርዳታ የሚያገኙ ቀዳሚ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ ለዓለም ሀገራት እርዳታ ከሚሰጡ በርካታ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ነች፡፡
ከፈረንጆቹ 1946 እስከ 2023 ድረስ ባሉት 75 ዓመታት ውስጥ አሜሪካ ቁልፍ እና ጥቅሜን ያስጠብቁልኛል ላለቻቸው ሀገራት ወታደራዊ ድጋፎችን አድርጋለች፡፡
እስራኤል፣ ግብጽ፣ ቬትናም፣ ደቡብ ኮሪያ እና አፍጋኒስታን ደግሞ በተጠቀሱት ዓመታት ከፍተኛውን የአሜሪካ እርዳታ ካገኙ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው?
እስራኤል ብቻ 312 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ከአሜሪካ አርዳታ በመቀበል ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን ቬትናም 184 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር፣ ግብጽ 183 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር፣ አፍጋኒስታን 157 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ደቡብ ኮሪያ ደግሞ 121 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ መቀበላቸውን ዩኤስ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በአጠቃላይ አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ150 ሀገራት ወታደራዊ እና የሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግ 960 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ ላለፉት 75 ዓመታት 4 ትሪሊዮን ዶላር በእርዳታ መልኩ ለ150 ሀገራት ለግሳለለች የተባለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 960 ቢሊዮን ዶላሩ ወታደራዊ እርዳታ ነው፡፡
ሀገሪቱ በ1949 ላይ 100 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ በመስጠት በታሪክ ከፍተኛ የእርዳታ ወጪ ያደረገችበት ዓመት ሲባል በ1997 ደግሞ በ25 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ዝቅተኛው ዓመት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
አሜሪካ እርዳታውን የምትሰጠው ወዳጅ እና ቁልፍ አጋር የተባሉ ሀገራት የተረጋጋ የጸጥታ ሁኔታ እንዲኖራቸው፣ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እና የሰው ሃይል ስልጠናን ለማስፋፋት፣ የኢኮኖሚ መረጋጋት እንዲኖር፣ የአሜሪካን ጥቅሞች እንዲከበሩ እና ሌሎችም ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡