በኢራቅ የሚገኙት የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች በሮኬት ተመቱ
የኢራን አጋር የሆነው የኢራቁ ታጣቂ ቡድን አሜሪካ እስራኤልን በመደገፍ በእስራኤል-ሀማስ ጦርነት የምትሳተፍ ከሆነ አሜሪካን ኢላማ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር
የኢራቅ መንግስት በጦር ሰፈሩ ዙሪያ ያለውን አካባቢ በመዝጋት ፍተሻ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
በኢራቅ የሚገኙት የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች በሮኬት እና በድሮን መመታታቸው ተገልጿል።
የአሜሪካን እና ሌሎች አለም አቀፍ ኃይሎችን የያዘው በምዕራብ ኢራቅ የሚገኘው አይን አል አሳድ የጦር ሰፈር በትናንትማው ምሽት በድሮን እና በሮኬት መመታቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የኢራቅ መንግስት በጦር ሰፈሩ ዙሪያ ያለውን አካባቢ በመዝጋት ፍተሻ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
በደረሰው ጥቃት ጉዳት ስለመድረሱ የታወቀ ነገር አለመኖሩን ዘገባው ጠቅሷል።
በባግዳድ አለምአቀፍ አየር መንገድ አካባቢ በሚገኘው በሌላኛው የአሜሪካ ወደታራዊ ካምፕ ላይም ጥቃት መድረሱን የገለጸው የኢራቅ ፖሊስ ስለጥቃቱ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም።
በኢራቅ የሚገኙት የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች በተደጋጋሚ በመጠቃት ላይ ናቸው።
ባለፈው ሮብዕ በአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ በተለያየ ጊዜ ሁለት የድሮን ጥቃቶች የደረሱ ሲሆን አንደኛው ጥቃት መጠነኛ የሆነ ጉዳት አድርሷል።
ባለፈው ሳምንት የኢራን አጋር የሆነው የኢራቁ ታጣቂ ቡድን አሜሪካ እስራኤልን በመደገፍ በእስራኤል-ሀማስ ጦርነት የምትሳተፍ ከሆነ በሮኬት እና ድሮን አሜሪካን ኢላማ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር።
አሜሪካ በኢራቅ 2000 ወታደሮች እና በጎረቤት ሶሪያ ደግሞ 900 ወታደሮች በመላክ በሁለቱም ሀገራት ጥቃት እየፈጸመ ያለውን አይኤስን እየተዋጋች ነው።