አዲስ መንግስት ለመመስረት የተቸገረችው ኢራቅ ለብሔራዊ ምክክር ጥሪ አቀረበች
የሃገሪቱ ፖለቲከኞች መንግስት ለመመስረት ውዝግብ ከጀመሩ 10 ወራት ተቆጥረዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዲሚ የፖለቲካ መሪዎች ዛሬ ረቡዕ ተገናኝተው እንዲመክሩ ጥሪ አቅርበዋል
አዲስ መንግስት ለመመስረት የተቸገረችው ኢራቅ ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ ጥሪ አቀረበች፡፡
ጥሪው በጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዲሚ የቀረበ ነው፡፡ አል ካዲሚ የሃገሪቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ መሪዎች ዛሬ ረቡዕ ተገናኝተው በጉዳዮች ላይ እንዲመክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢራቃውያን የሳዳም ሁሴን አገዛዝ በአሜሪካ ወረራ ካበቃበት ከፈረንጆቹ 2003 በኋላ አዲስ መንግስት ተመስርቶ ለማየት የሚያስችሉ የተለያዩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ነበር፡፡
በተለይ በደቡባዊና ምዕራባዊ የሃገሪቱ አካባቢዎች ከ2019 ጀምሮ ሲደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች ፍሬ አፍርተው ለ5ኛ ጊዜ ባሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት መባቻ ነበር ጠቅላላ ምርጫን ለማካሄድ ተችሎ ነበር፡፡ ሆኖም የምርጫው አሸናፊዎች መንግስት ለመመስረት ሳይችሉ ቀርተው 10 ወራትን አስቆጥረዋል፡፡
የሺዓው መሪ ሞክታዳ አል ሳድር ምርጫውን በአብላጫ ድምጽ ቢያሸንፉም መንግስት ለመመስረት አለመቻላቸው የሚታወስ ነው፡፡
በፖለቲከኞቹ በተለይም በሺዓ ሙስሊመቹ መካከል ያለው የከረረ ልዩነት መንግስት ለመመስረት አለማስቻሉ ነው የሚነገረው፡፡ መካረሩ ሃገሪቱን ለዳግም ግጭት እንዳይዳርጋትም ተሰግቷል፡፡
ጉዳዩ ያሳሰባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዲሚም ትናንት ማክሰኞ ሃገራዊ ምክክርን ለማድረግ የሚያስችል ጥሪን ለፖለቲከኞች አቅርበዋል፡፡
ካዲሚ ፖለቲከኞቹ በጥብቅ ወደሚጠበቀውና ባግዳድ ወደሚገኘው ብሔራዊ ቤተ መንግስት (ግሪን ዞን) መጥተው እንዲነጋገሩ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ስብሰባው ላጋጠሙት ፖለቲካዊ ቀውሶች መፍትሔ ለማበጀት የሚያስችሉ መደላድሎችን ለመጣል በማሰብ የተጠራ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ የፖለቲከኞቹ አካሄድ ስክነት የተሞላበትና መደማመጥ ያለበት ሊሆን እንደሚገባም ካዲሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡