አሜሪካ ወደ አየር ክልሏ ገብቷል ያለችው ምንነቱ ያልታወቀ ነገር መትታ መጣሏን ገለጸች
አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት የቻይና ተንሳፋፊ ፊኛን መትታ መጣሏ ይታወሳል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የዋሽንግተን አየር ክልል ጥሶ የገባው አካል እንዲመታ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል ተብሏል
አሜሪካ ወደ አየር ክልሏ ገብቷል ያለችው ምንነቱ ያልታወቀ ነገር መትታ መጣሏን ገለጸች።
አሜሪካ የአየር ክልሏን ጥሶ የገባ አንድ ምንነቱ እና ባለቤቱ ያልታወቀ ቁስን መትቼ ጥያለሁ ብላለች።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ የአሜሪካ አየር ሀይል በካናዳ ድንበር አቅራቢያ በአላስካ ግዛት በኩል የአየር ክልሏን ጥሶ የገባ ምንነቱ ያልታወቀ አካል መትቷል።
የሀገሪቱ አየር ሀይል ምንነቱ ያልታወቀው ቁስ ሰው አልባ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ እና ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዲመታ ትዕዛዝ ካስተላለፈ በኋላ መመታቱን የፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ተናግረዋል።
አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት ንብረትነቱ የቻይና የሆነ ተንሳፋፊ ፊኛ ወደ አየር ክልሌ ገብቶ እየሰለለኝ ነው በሚል መምታቷ ይታወሳል።
ቻይና በበኩሏ ወደ ዋሽንግተን የአየር ክልል የገባው ተንሳፋፊ ፊኛ የአየር ንብረት መረጃዎችን የሚሰበስብ እንጂ ስለላ አልነበረም ስትል ምላሽ ሰጥታለች።
አሜሪካ በዚህ ተንሳፋፊ ፊኛ ምክንያትም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ቻይና ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ አራዝመዋል።
ቻይና ለስለላ በሚል አሜሪካንን ጨምሮ ወደ አምስት አህጉራት ተንሳፋፊ ፊኛዎችን እንደላከች ዋሽንግተን አስታውቃለች።