አሜሪካ ለእስራኤል እያደረገች ያለው ወታደራዊ ድጋፍ ምን ምን አካቷል?
ዋሽንግተን ለቴል አቪቭ እጅግ ዘመናዊ የጦር ጄቶችን ከመላክ ባሻገር ሚሳኤሎችን በአየር ላይ የሚያደባዩ መቃወሚያዎችን እንድትሰራ ደጋፍ እያደረገችላት ነው
አሜሪካ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ከፍተኛውን እርዳታ የምታደርገው ለእስራኤል ነው
የጋዛው ጦርነት ሰባተኛ ወሩን መያዙን ተከትሎ አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ እንድታቋርጥ የሚጠይቁ ድምጾች እየተበራከቱ ነው።
የባይደን አስተዳደር ለቴል አቪቭ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ከማድረግ እንዲቆጠብ የአሜሪካ ባለስልጣናት መጠየቃቸውንም ቀጥለዋል።
ይሁን እንጂ እስራኤል እንደሀገር ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ ከአሜሪካ ጋር የመሰረተችው ጠንካራ ግንኙነት ሻክሮ ወታደራዊ ድጋፍ እስከማቋረጥ ደርሶ አልታየም።
አሜሪካ እና እስራኤል በፈረንጆቹ 2016 ለሶስተኛ ጊዜ ለአስር አመት የሚቆይ የወታደራዊ ትብብር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
በዚህ ስምምነት መሰረት እስራኤል ከ2018 እስከ 2028 ድረስ 38 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ታገኛለች፤ 33 ቢሊየን ዶላሩ ለጦር መሳሪያ ግዥ ቀሪው ደግሞ ለጸረ ሚሳኤል ስርአት ግንባታ እንደሚውል መስማማታቸውን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
ይህም እስራኤል ከአሜሪካ በየአመቱ ከፍተኛውን ወታደራዊ ድጋፍ የምታገኝ ሀገር አድርጓታል።
እስራኤል እንደ ሀገር ከተመሰረተችበት 1948 ጀምሮ ከአሜሪካ ወደ እስራኤል የተላከው ድጋፍም 330 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ ነው የሚገመተው።
እስራኤል ከአሜሪካ ያገኘቻቸው ድጋፎች
“ኤፍ-35” የተሰኘውን እጅግ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላን ከአሜሪካ ቀጥላ የታጠቀችው እስራኤል ናት።
እስራኤል በአሜሪካ ድጋፍ 75 “ኤፍ-35” ጄቶችን ለማስገባት ባለፈው አመት ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን፥ እስካሁን 36ቱ ቴል አቪቭ ደርሰዋል ተብሏል።
እስራኤል ከሃማስም ሆነ ከሄዝቦላህ የሚወነጨፉ ሚሳኤሎች እንደብዛታቸው የዜጎቿን ህይወት እንዳይቀጥፉ ያደረገው “አይረን ዶም” የተሰኘው የጸረ ሚሳኤል ስርአቷ ነው።
በፈረንጆቹ 2006 እስራኤልና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ የድንበር ጦርነት ሲጀምሩ አሜሪካ ለእስራኤል ድጋፍ በማድረግ የአጭር ርቀት ሚሳኤሎች መቃወሚያው (“አይረን ዶም”) ተሰርቷል።
ቴል አቪቭ የሚሳኤል መቃወሚያ ስርአቷ እንዲዘምን በየአመቱ ከዋሽንግተን በሚሊየን ዶላር የሚቆጠር ድጋፍ ታገኛለች።
ከዚህም ባሻገር እስራኤል ከ100 እስከ 200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚወነጨፉ ሮኬቶችን መጥቶ የሚጥል “ዴቪድ ስሊንግ” የተሰኘ የሚሳኤል መቃወሚያ ስርአት እንዲኖራት ከዋይትሃውስ ሹማምንት የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላታል።
እስራኤል ከስድስት ወራት በፊት ሃማስ ድንበሯን ጥሶ ጥቃት ካደረሰባት በኋላ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላም የዋሽንግተን ድጋፍ ይበልጥ ተጠናክሯል።
ከ21 ሺህ በላይ ሚሳኤሎችና ሮኬቶች፣ ከ200 በላይ ድሮኖች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ቦምቦች እና ተተኳሽ ጥይቶች ወደ ቴል አቪቭ ተልከዋል።
ዋሽንግተን በመካከለኛው ምስራቅ ዋነኛ አጋሯን ለመጠበቅም አውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ መርከቧን መላኳ ይታወሳል።
በጋዛ አስገዳጅ የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳብ እንዳይተላለፍ በጸጥታው ምክርቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ አጋርነቷን ማሳየቷም አይዘነጋም።
የባይደን አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እስራኤል በጋዛ ንጹሃንን መጠበቅ አልቻለችም በሚል እየወቀሰ ነው።
በመጋቢት ወር የጸጥታው ምክርቤት በጋዛ ተኩስ እንዲቆም በቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ድምጽ ሲሰጥም አሜሪካ ተአቅቦን መምረጧ ቴል አቪቭን ማስቆጣቱ ይታወሳል።
ተንታኞች ግን በወቅቱ ከሁለቱም ጎራ ሲነሳ የነበረው ቅሬታ ከሚዲያ ፍጆታ አያልፍም፤ ሀገራቱ ወትደራዊ ትብብራቸው ቀጠናዊ ፋይዳውም ከፍ ያለ በመሆኑ በቀላሉ የሚሸረሸር አይደለም ይላሉ።