ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው የአሜሪካን እዳ በ8 ትሪሊየን ዶላር መጨመራቸው ይታወሳል
የአሜሪካ ብሄራዊ እዳ ከ36 ትሪሊየን ዶላር መሻገሩ ተነገረ።
የአሜሪካን እዳ የሚመዘግበው ድረገጽን ጠቅሶ አርቲ እንዳስነበበው የአሜሪካ እዳ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የ2 ትሪሊየን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል።
የልዕለ ሀያሏ ሀገር እዳ ከጥር እስከ ህዳር 2024 በ6 በመቶ መጨመሩና በአራት ወራት ውስጥ በ1 ትሪሊየን ማደጉንም ዘገባው ጠቅሷል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት የሀገሪቱ ብሄራዊ እዳ ከ35 ትሪሊየን ዶላር ማለፉን ያስታወቀው በሀምሌ ወር እንደነበር ይታወሳል።
ትናንት ይፋ ስለተደረገው የ36 ትሪሊየን ዶላር ግን የአሜሪካ ግምጃ ቤት እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።
የአሜሪካ ብሄራዊ እዳ በ2027 ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ (ጂዲፒ) 106 በመቶ እንደሚደርስ የኮንግረንሱ የበጀት ጽህፈት ቤት በነሃሴ ወር ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።
አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) በበኩሉ “አሁን ባለው ፖሊሲ አጠቃላይ የመንግስት እዳው በ2032 ከጂዲፒው 140 በመቶ በላይ ይሆናል” ብሏል።
የአሜሪካ እዳ መጨመርና ከጂዲፒው አንጻር ያለው ምጣኔ እያሻቀበ መሄድ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለአለም ምጣኔሃብት አደጋ መደቀኑንም ነው ተቋሙ ያሳሰበው።
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ በቅርቡ የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች የሚጠግኑ እና በፍጥነት የሚያድገውን ብሄራዊ እዳ መቆጣጠር የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ይጠበቃል።
ተንታኞች በትራምፕ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን የአሜሪካ እዳ በ8 ትሪሊየን ዶላር መጨመሩን ያወሳሉ።
ሀገሪቱ በየአመቱ ለእዳዋ ወለድ 1 ትሪሊየን ዶላር ትከፍላለች፤ ይህ ወለድ ባይኖር ለእያንዳንዱ አሜሪካዊ ዜጋ የ3 ሺህ ዶላር የታክስ ቅነሳ ማድረግ ይቻል ነበር።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ ብሄራዊ እዳ 36 ትሪሊየን ዶላር ደርሶ እያንዳንዱ ዜጋ ከ100 ሺህ ዶላር በላይ እዳ እንዲኖርበት ሆኗል ነው የተባለው።