አሜሪካ የአይቲ ባለሙያው ያለበትን ለጠቆመኝ 10 ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ አለች
ቻይናዊው የአይቲ ባለሙያ ከ81 ሺህ በላይ ቁልፍ መረጃዎችን ከአሜሪካ ኩባንያዎች በበይነ መረብ ጥቃት መንትፏል ተብሏል
ወጣቱ የመነተፋቸውን መረጃዎች ለቻይና ኩባንያዎች እንደሸጠ ተገልጿል
አሜሪካ የአይቲ ባለሙያው ያለበትን ለጠቆመኝ 10 ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ አለች፡፡
ጉዋን ቲያንፌንግ የተሰኘው የ30 ዓመት ወጣት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ሲሆን በቻይናዋ ሲቹዋ ግዛት ይኖራል፡፡
ይህ ወጣት ሲቹዋን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባያ ተቀጥሮ የሚሰራ ባለሙያ ሲሆን በፈረንጆቹ 2020 ላይ በአሜሪካ ኩባያዎች ላይ ከባድ የበይነ መረብ ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል፡፡
ወጣቱ ባደረሰው ጥቃት ምክንት 81 ሺህ ቁልፍ የሚባሉ መረጃዎችን መንትፏል የተባለ ሲሆን የአሜሪካ ቁልፍ ተቋማት ደግሞ የጥቃቱ ዋነኛ ሰለባ እንደሆኑ ኤፍቢአይ በድረገጹ ላይ አስፍሯል፡፡
እንዲሁም ይህ ወጣት የመነተፋቸውን ቁልፍ መረጃዎች ለቻይና የቢዝነስ እና መንግስታዊ ተቋማት አሳልፎ እንደሰጠም ተገልጿል፡፡
ወጣቱ ከመነተፋቸው መረጃዎች ውስጥም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይይለፍ ቃሎች፣ ጠቃሚ መረጃዎች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የወጣቱ ቀጣሪ ኩባንያ ግለሰቡን አሳልፎ እንዲሰጥ ከአሜሪካ ለቀረበለት ጥያቄ ባለሙያው የት እንዳለ እንደማያውቅ መናገሩን ተከትሎ ማዕቀብ ተጥሎበታል፡፡
በመሆኑም አሜሪካ ይህ ወጣት ያለበትን ለጠቆመኝ 10 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ እንደምትሰጥ አስታውቃለች፡፡