የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅምች
የአለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ሀገር ለመሪዎቿ የምትከፍለው ክፍያ ከአንዳንድ መካከለኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ያነሰ ነው
የአሜሪካ መሪዎች ከጉዞ እስከ መዝናኛ፣ የምግብ እና የቤት ወጪያቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል
ከሀገራቸው አልፈው አለምን ይመራሉ የሚባሉት የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ የአለም መሪዎች ቀዳሚዎቹ ቢሆኑም እንደ ሌሎች ሠራተኞች ደመወዝ የሚቀበሉ የፌዴራል ተቀጣሪዎች ናቸው።
ይህ ደሞዝ ከአብዛኛዎቹ የስራ አይነት እና መካከለኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መሪዎች ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ነው ቢባልም፤ ስልጣኑ የሚሰጠው የገንዘብ ጥቅማጥቅም በርካታ ነው፡፡
ነጻ መኖሪያ ቤት፣የምግብ፣ ጉዞ ፣ ጡረታ እና ደህንነት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ጥቅማጥቅሞች ከማንኛውም መደበኛ ስራ በተለየ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡
በ2001 የአሜሪካ ግምጃ ቤት ለኮንግረሱ ባቀረበው ረቂቅ መሰረት በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አመታዊ ደመወዝ 400 ሺ ዶላር ነው።
ከዚህ ቀደም ብሎ ለ30 አመታት የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ደመወዝ 200ሺ ዶላር የነበረ ሲሆን፤ ስራው በአለም ላይ ካሉ በጣም ከባድ እና ወሳኝ የሰራ ዘርፎች መካከል አንዱ በመሆኑ ከ23 አመት በፊት የተሸሻለው ደምዎዝ ለስራው ያለውን አክብሮት ለማሳየት የተደረገ ነው፡፡
ከደመወዙ በተጨማሪ ፕሬዝዳንቱ ለግል ወጪ 50ሺ፣ ለመዝናኛ 19 ሺ እና ለጉዞ ከቀረጥ ነጻ 100 ሺህ ዶላር ይመደብለታል፡፡
አዲስ የሚመረጥ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነጩ ቤት መንግስትን ለማስዋብ እና አዳዲስ ፈርኒቸሮችን ለመግዛት ተጨማሪ 100 ሺ ዶላር ያገኛል፡፡
ፕሬዝዳንቶች የሚኖሩበት ነጩ ቤትመንግስት 4 ሚሊየን ዶላር በአመት ያስፈልገዋል። ይህ ወጪ በመንግስት የሚሸፈን ሲሆን ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ በግሉ ለሚያዘጋጃቸው ድግሶች ለጽዳት እና መስተንግዶ ስራ ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች ወጪን ራሱ ይሸፍናል፡፡
“ማሪን ዋን” ሄሊኮፕተርን ጨምሮ የአሜሪካ መሪ የሚጠቀምበት “ቦይንግ 747-200 ቢ” አውሮፕላንን ለማንቀሳቀስ በሰአት 200 ሺ ዶላር ይጠይቃል፡፡
በስልጣን ላይ እና ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ጥበቃ የሚያደርገው የደህንነት ተቋም “ሴክሬት ሰርቪስ” በአመት በአጠቃላይ 1.9 ቢሊየን ዶላር በጀት የተመደበለት ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከቢሮ ከተሰናበተ በኋላም በስራ ላይ ከሚገኝ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደምዎዝ እኩል የጡረታ ክፍያ ያገኛል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና የዘንድሮው የሪፐብሊካን እጩ ዶናልድ ትራምፕ በአሁኑ ወቅት 230ሺ ዶላር ጡረታ በአመት ይከፈላቸዋል፡፡
የምክትል ፕሬዝዳንቱ ደመወዝ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ወይም በታክስ ሕጉ ውስጥ በግልጽ ቁጥር አልተቀመጠም፤ ክፍያው ተለዋዋጭ እና ከኑሮ ውድነት ጋር እየተስተካከለ የሚጨመር ቢሆንም አሁናዊው ቁጥር በአመት 235 ሺህ ዶላር እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በትራምፕ የስልጣን ዘመን ይህ ክፍያ ወደ 243 ሺ ዶላር ከፍ እንዲል ተጠይቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የነጩ ቤት ፕረስ ሴክረተሪ (ቃል አቀባይ) ከፍተኛ ክፍያ ከሚያገኙት የአሜሪካ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ሲሆን 180 ሺህ ዶላር ደግሞ አመታዊ ክፍያቸው ነው፡፡