አሜሪካ የውጭ እርዳታ ለማቆም መወሰኗን የሚያመላክት ሰነድ አፈትልኮ ወጣ
ውሳኔው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እና ለእስራኤልና ግብጽ የሚደረግ ወታደራዊ ድጋፍን አያጠቃልልም ተብሏል
የአለማችን ቀዳሚዋ የእርዳታ ለጋሽ ሀገር አሜሪካ በ2023 የ68 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓ ተገልጿል
የአሜሪካ መንግስት ነባር እና አዳዲስ የውጭ እርዳታን ለማቁም መወሰኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ ሀገራት ለሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች የላከው የውስጥ ማስታወሻ አሳየ።
አፈትልኮ የወጣው ማስታወሻ ፕሬዛንት ትራምፕ ባለፈው ሰኞ ለ90 ቀናት የውጭ የልማት ድጋፎች እንዲቆሙ ያሳለፉትን የስራ አሰፈጻሚ ትዕዛዝ የተከተለ ነው ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
የአለማችን ቀዳሚዋ የእርዳታ ለጋሽ ሀገር አሜሪካ በ2023 የ68 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን የሀገሪቱ መንግት መረጃ ያሳያል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ የላከው ማስታወሻ ሁሉም የልማት እና ወታደራዊ ድጋፎች መቆማቸውን ያሳያል።
አስቸኳይ የምግብ እርዳታ፣ ለእስራኤልና ግብጽ የሚደረገው ወታደራዊ ድጋፍ ግን እንደሚቀጥል በሰነዱ ላይ መመላከቱን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
"አዲስ እርዳታ ለመልቀቅም ሆነ የነበሩትን ለማራዘም ግምገማ ተካሂዶ መጽደቅ ይኖርበታል" ይላል አፈትልኮ የወጣው ማስታወሻ።
ግምገማው ተካሂዶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውሳኔ እስኪያስተላልፍ ድረስ የአሜሪካ ባለስልጣናት ከእርዳታዎች ጋር የተያያዙ ስራዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ትዕዛዝ መስጠት እንዳለባቸውም ይጠቅሳል።
ሁሉም የውጭ እርዳታዎች ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግቦች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ለማረጋገጥም በ85 ቀናት ውስጥ ሰፊ ግምገማ እንዲካሄድም ያዛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ አሜሪካ የውጭ እርዳታ ማድረግ ያለባት ሀገሪቱን "ጠንካራ፣ ደህንነቷ የተጠበቀና የበለጸገች" እንድትሆን የሚያስችል ብቻ ከሆነ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
አሜሪካ ቀዳሚዋ የውጭ እርዳታ ላኪ ሀገር እንደመሆኗ ጊዜያዊ ውሳኔው በአሜሪካ ድጋፍ በሚደረግላቸው የእርዳታ ድርጅቶች ላይ ተጽዕኖው ከፍ ያለ እንደሚሆን ይገመታል።
በባይደን አስተዳደር የቢሊየን ዶላሮች ድጋፍ ስታገኝ የቆየችው ዩክሬንም በውሳኔው ክፉኛ ትጎዳለች ብሏል ኤኤፍፒ በዘገባው።
በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ለከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ በተጋለጠችው ጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ በየቀኑ ከ600 በላይ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መግባት በጀመሩበት ወቅት ነው ዋሽንግተን የውጭ እርዳታ በጊዜያዊነት እንዲቆም የወሰነችው።
በሱዳን እና በሌሎች ጦርነት ባደቀቃቸው ሀገራት ሚሊየኖች አስቸኳይ ድጋፍ ይሻሉ።
አፈትልኮ የወጣው ሰነድም የአሜሪካ መንግስት የውጭ እርዳታ እንዲቋረጥ ሲወሰን አስቸኳይ የምግብ እርዳታን አለማካተቱ ተስፋን ቢሰጥም የበርካታ የእርዳታ ድርጅቶች ስራ እንደሚታወክ ይጠበቃል።