አሜሪካ ለእስራኤል 8 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ማቀዷን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናገሩ
የሽያጭ እቅዱ በቅርቡ ሴኔቱ እንዲያጸድቀው ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል
በአይነቱ ከፍተኛ የተባለለት የጦር መሳሪያ ሽያጭ የውጊያ ጄቶችን ጨምሮ የነፍስወከፍ ጦር መሳሪያዎችን ያካትታል
አሜሪካ ለእስራኤል 8 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ማቀዷን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለእስራኤል የሚደረገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ አስመልክቶ ለኮንግረሱ ማሳወቁን ባለስልጣናቱ በትላንትናው ዕለት ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ የእስራኤል ዋነኛ አጋር ሆና መቀጣሏን አመላካች ነው የተባለው እቅድ ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በሴኔቱ መጽደቅ ይጠበቅበታል፡፡
ሮይተርስ አክሲዎስን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ የመሳሪያ ሽያጩ ተዋጊ ጄቶች ፣ ሄሊኮፕተሮች ፣ የመድፍ እና የታንክ ተተኳሾን እንዲሁም ሌሎች የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን እንደሚያካትት ጠቅሷል፡፡
2.3 ሚሊዮን ህዝብ ያፈናቀለ፣ የረሃብ ቀውስ ያስከተለው እና በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነው እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ጦርነት ዋሽንግተን አለም አቀፋዊ ትችቶችን እየተጋፈጠች ትገኛለች፡፡
ይህኛው የጦር መሳሪያ ሽያጭም እስራኤል በጋዛ በንጹሀን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት እንዲበረታ የሚያደርግ ነው በሚል የተለያዩ በሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና በመብት ተሟጋቾችች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ 15 ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት ከ45 ሺ በላይ ንጹሀን መሞታቸውን እና በፍርስራሾች ውስጥ የተቀበሩ አድራሻቸው የጠፉ ሰዎች እንዳሉ ይጠቅሳል፡፡
ከዚህ ቀደም በጋዛ የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ በ30 ቀናት ውስጥ ካልተሻሻለ የጆ ባይደን አስተዳደር ለእስራኤል የሚያደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ እና ድጋፍ እንደሚያቋርጥ ዝቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
30 ቀናቱ ሲጠናቀቅ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች በጋዛ የሚገኝው የሰብአዊ ድጋፍ ስርጭት እምብዛም እንዳልተሻሻለ እየገለጹ ባሉበት ዋሽንግተን ለቴልአቪቭ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል አስታውቃለች፡፡
ከ16 ቀናት በኋላ ከስልጣን የሚለቁት ባይደንም ሆኖ እሳቸውን የሚተኩት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጠንካራ የእስራኤል ደጋፊዎች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው የጋዛን ጦርነት ስልጣን ከመያዛቸው በፊት እንደሚያስቆሙ የተናገሩት ትራምፕ እስካሁን ለውሳኔ የቀረበ የድርድር ሂደትን ገቢራዊ ሲያደርጉ አልታዩም፡፡
በሌላ በኩል በትላንተናው ዕለት እስራኤል በጋዛ ታግተው የሚገኙ ዜጎችን ለማስለቀቅና የተኩስ አቁም ድርድሩን ዳግም ለማስጀመር ልኡኳን ወደ ኳታር ልትልክ ስለመሆኑ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በኳታር በቅርቡ ዳግም ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ድርድር ተሰናባቹ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ካቀረቡት ምክረሃሳብ ጋር የተቀራረበ መሆኑን ሲኤንኤን ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።