ጤና ሚኒስቴር ምርጫ ማድረግ እንደሚቻል ምክረ ሃሳብ አቀረበ
ኮቪድ-19 የጤና ስጋት አለመሆኑ ከተረጋገጠ ከ9-12 ወራት ጊዜ ዉስጥ ምርጫ እንዲካሔድ መወሰኑ ይታወቃል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ላይ እየተወያየ ነው
ጤና ሚኒስቴር ምርጫ ማድረግ እንደሚቻል ምክረ ሃሳብ አቀረበ
የጤና ሚኒስቴር በኮሮና ምክንያት የተራዘመው ሀገራዊ ምርጫ መደረግ እንደሚችል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ አቀረበ፡፡
ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አገራዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ሲሉ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት አመለክተዋል። ዶ/ር ሊያ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት መሰብሰቢያ አደራሽ
እያደረገ ባለው 5ኛ ዓመት 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባው እየተወያየ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ምንም እንኳን ቫይረሱ አሁንም በኢትዮጵያ የጤና ስጋት ቢሆንም ስጋትነቱ ቀደም ሲል ከነበሩት ትንበያዎች አንጻር ከፍተኛ አለመሆኑን ፣ ኮቪድ-19 ረዘም ላለ ጊዜ አብሮን ሊቆይ የሚችል መሆኑን ፣ ስለስርጭቱ የተሸለ መረጃ መኖሩን እንዲሁም ቀደም ሲል ከነበረበት በተሻለ የመከላከል ሁኔታዎች መኖራቸውን ሚኒስቴሩ በምክንያትነት አቅርቧል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት አጭር ሪፖርት ኮቪድ-19 መከላከልን ከግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ስነምግባር፣ ደንብና ማስፈፀሚያ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ሃገራዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብለዋል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የወረርሽኝ ስርጭት ከተከሰተ በተለየ ሁኔታ መታየት ሊያስፈልገው እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ዶ/ር ሊያ ባቀረቡት ሪፖርት ማመልከታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህ ቀደም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከምርጫ መራዘም ጋር በተያያዘ ባሳለፈው የመጨረሻ ዉሳኔ ኮቪድ-19 የቴና ስጋት አለመሆኑ በጤና ሚኒስቴር እና በሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ማረጋገጫ ከተሰጠ ከ9 እስከ 12 ወራት ባለው ጊዜ ዉስጥ ምርጫው እንዲካሔድ መወሰኑ ይታወቃል፡፡