የስራ ሰዓታችን ተጠናቋል በሚል ራሱን በማጥፋት ላይ የነበረ ሰው ለመርዳት ፈቃደኛ ያልሆኑት የአሜሪካ ፖሊሶች ከስራ ተሰናበቱ
ፖሊሶቹ አጋጣሚውን አይተው እንዳላዩ ከስፍራው ሲሸሹ በሌላ ፖሊስ የሰውነት ካሜራ እይታ ውስጥ ገብተዋል
ድርጊቱ በተፈጸመበት መናፈሻ አቅራቢያ የነበሩ ሁለት የሴንት ሊዊስ ሚዙሪ ፖሊሶች ከስራ ተሰናብተዋል
የስራ ፈረቃቸው በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ ራሱን በማጥፋት ላይ የነበረ ግለሰብን ህይወት ለመታደግ ፈቃደኛ ያልሆነት ፖሊሶች ጉዳይ በአሜሪካ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡
ኦስቲን ፍሬዘር እና ታይ ዋረን የተባሉት የሴንት ሉዊስ ፖሊስ አባላት ወደ 911 ተደውሎ ኡራያን ሮድሪጌዝ ሪቬራ የተባለ ወጣት ራሱን ሊያጠፋ እንደሆነ የአደጋ ጥሪ ይደርሳቸዋል፡፡
የአደጋ ጥሪው ከተሰማ ከደቂቃዎች በኋላ ፍሬዘር እና ዋረን የተባሉት ፖሊሶች ሮድሪጌዝሪቬራን በሴንት ሉዊስ የደን መናፈሻ ውስጥ ጭንቅላቱ በጥይት ተመቶ ሲያጣጥር ያገኙታል፡፡
ፖሊሶች በአደጋው ስፍራ ከደረሱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ ዋረን የ29 አመቱ ሮድሪጌዝ አሁንም በህይወት እንዳለ እና ወደ ሆስፒታል ሊወስዱት እንደሚገባ ለባልደረባው ሲነግረው በሰውነት ላይ በሚገጠም ካሜራ ላይ በተቀረጸ ድምጽ ይሰማል፡፡
በአደጋው ስፍራ ቀድሞ እንደደረሰ የህግ አካል አካባቢውን መከለል እና ከንክኪ ማራቅ እንዲሁም ግለሰቡን ወደ ሆስፒታል መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህን ማድረግ የሚወስደውን ረጅም ጊዜ የሚያውቀው ፍሬዘር የተባለው ሌላኛው ፖሊሲ ከ30 ደቂቃ በኋላ ፈረቃው እንደሚጠናቀቅ እና ሌሎች ፖሊሶች ተጎጂውን እስኪያገኙት ተዘዋውረው እንዲመጡ ለባልደረባው ምላሽ ሲሰጥ ተደምጧል፡፡
ቀጥሎም ከዛፍ ስር ተደግፎ ህይወቱ ሳያልፍ በሲቃ እያጣጣረ የነበረውን የ29 አመት ወጣት ለመርዳት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ አካባቢውን ጥለው ሄደዋል፡፡
ብዙም ሳይቆይ በስፍራው የደረሰው ሶስተኛ ፖሊስ ዋረን እና ፍሬዘር የተጎዳው ሰው አቅራቢያ ደርሰው ምንም አይነት እርዳታ ሳያደርጉለት ከአከባቢው ሲሄዱ በሰውነት ካሜራው ቀርጿቸዋል፡፡
ሁለቱ ፖሊሶች ከ10 ደቂቃ በኋላ ድጋሚ ወደ ስፍራው በመመለስ በአካባቢው ለነበሩ ፖሊሶች ለአደጋው አዲስ መሆናቸውን እና ምንም እንደማያውቁ ሆነው ለመቅረብ ሲያስመስሉም ታይተዋል፡፡
ደይሊ ሜይል እንዳስነበበው በራሳቸው የሰውነት ካሜራ እና እነርሱን ተከትሎ በአካባቢው በደረሰው ፖሊስ ካሜራ ማስረጃነት ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት እና በቸልተኝነት ሁለቱም ፖሊሶች ከስራቸው ተሰናብተዋል፡፡
አጋጣሚው በመገናኛ ብዙሀን ሰፊ ሽፋን ማግኝቱን ተከትሎ በፈጠረው ህዝባዊ ቁጣ ፖሊሶቹ ለፈጸሙት ጥፋት ከስራ ከማባረር ባለፈ በወንጀል እንዲጠየቁ በርካታ ሰዎች እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡