86 የአሜሪካ ፖሊሶች ራሳቸውን ማጥፋታቸው ተገለጸ
የስራ ጫና እና ፖሊሶችን በጨካኝነት የመሳል አመለካከት መጨመር እያደገ እንደሆነ ተገልጿል
በአሜሪካ ራሳቸውን የሚያጠፉ ፖሊሶች ቁጥር እየጨመረ ነው ተብሏል
በአሜሪካ ራሳቸውን የሚያጠፉ ፖሊሶች ቁጥር ማሻቀቡ ተገለጸ።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር በሆነችው አሜሪካ ራስን የማጥፋት ወንጀል እየጨመረ መሆኑ ተገልጿል።
የሀገሪቱ ፖሊሶች ከተቀረው አሜሪካዊያን ዜጎች ጋር ሲነጻጸሩ 50 በመቶ ራሳቸውን ለማጥፋት የተጋለጡ ሆነው ተገኝተዋል ተብሏል።
እንደ ሲኤን ኤን ዘገባ ከሆነ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ አራት ፖሊሶች በታጠቁት የጦር መሳሪያ ራሳቸውን ተኩሰው እንደገደሉ ተገልጿል።
ይህም በተያዘው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት ውስጥ ብቻ ህግ ለማስከበር በታጠቁት የጦር መሳሪያ ራሳቸውን ያጠፉ ፖሊሶችን ቁጥር ወደ 86 ከፍ አድርጎታል ተብሏል።
አንድ የአሜሪካ ፖሊስ በሳምንት ከ70 ሰዓት በላይ ጊዜ በስራ ላይ እንዲያሳልፉ ይገደዳሉ የተባለ ሲሆን ይህም ከፍተኛ የስራ ጫና እያደረሰባቸው እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ራስን ማጥፋት ወይም ራስን ለማጥፋት መሞከር ከአዕምሮ ህመም አይነቶች መካከል አንዱ ነው የተባለ ሲሆን ይህም በስራ ጫና እና ከስራ ጋር የተገናኙ ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ለአሜሪካ ፖሊሶች ራስን ማጥፋት ትልቁ ምክንያት የተባለው ሌላኛው ምክንያት አሰቃቂ የሆኑ ወንጀሎች እየተበራከተ መምጣት ዋነኛው እንደሆነ ተገልጿል።
በተለይም ባንድ ጊዜ በአሜሪካ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች ፖሊሶችን ለከፋ የአዕምሮ ህመም ዳርገዋል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም በአሜሪካ እየጨመረ መጥቷል የተባለው ፖሊሶችን እንደገዳይ እና ጨካኝ አድርጎ የመሳል አመለካከቶች ፖሊሶች ስራቸውን እና ራሳቸውን እየጠሉ እንዲመጡ ማድረጉ ተገልጿል።
እንዲሁም የአሜሪካ ፖሊስ አመራሮች ለአዕምሮ ህመም እና ምልክቶች ትኩረት እየሰጡ አይደለም የተባለ ሲሆን የስራ ጫናዎችን እንዲረዱም ባለሙያዎች አሳስበዋል።