ጋዜጠኛው ”ሀሳብን ከመግለጽና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ ከመጻፍ ባለፈ ምንም ወንጀል አልፈጸምኩም” ሲል ክሱን ተከላክሏል
መንግስት በእስር ላይ የሚገኘውን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን መክሰሱን የጋዜጠኛው ጠበቃ ተናገሩ፡፡
ክሱን በንባብ ያሰማው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረሽብርና የሕገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው። በጋዜጠኛው ላይ ክሱ ትናንትና የተከፈተ ሲሆን ክሱ ዛሬ ለተከሳሽ ደርሶ በችሎት መነበቡን ጠበቃው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ዐቃቤ ሕግ ጋዜጠኛው ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ በሚሰራበት ፍትሕ መጽሔት በተለያዩ የህትመት ቀናት ” የመከላከያ ሰራዊትን ሚስጥራዊ ተግባራትን በማውጣትና እና ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት”በሚል ነው የከሰሰው፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ሀሳብን ከመግለጽና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ ከመጻፍ ባለፈ ምንም ወንጀል ፈጽሞ እንደማያውቅ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው የመንግስት ሥርዓት ታስሮ ዋስትና ተፈቅዶለት፤ ለሶስት ዓመታት ሕግን አክብሮ እየተመላለሰ ፍርድ ቤት ይቀርብ እንደነበርም ጠበቃው አቶ ሄኖክ አንስተዋል፡፡
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ደንበኛቸው በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ሕግ አንቀጽ 67/ሀ እና በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 6 መሰረት የዋስትና መብቱ መጠየቃቸውን እንዲጠበቅለት ጠይቀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ከሀገር እንዲወጣ በተለያዩ አካላትና መንግስታት ሳይቀር ግፊት ቢደረግበትም ጋዜጠኛው ግን “ስራዬና ሞቴ በሀገሬ ላይ ነው” ብሎ ከሀገር ሳይወጣ መቅረቱን ጠበቃው ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ቋሚ አድራሻ ያለውና ህግን የሚያከብር በመሆኑፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱን እንዲፈቅድለት ጠበቃው ጠይቀዋል፡፡ ዐቃቢህግ ግን ጋዜጠኛው በተደራራቢ ክስ በመከሰሱና በልዩ ሁኔታ ዋስትና ሊያስከለክል እንደሚችልና የሰበር ውሳኔ ድንጋጌዎች ዋስትናን ሊያስከለክል እንደሚችል ጠቅሶ ዋስትና ሊሰጥ አይገባም ብሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በዋስትናው ላይ ብይን ለመስጠት ለአርብ ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች መለስ ዜናዊና ኃይለማሪያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመን መታሰሩ ይታወሳል፡፡ጋዜጠኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የታሰረ ሲሆን ክስ ሲመሰረትበት ግን የመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡