አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ተሸሙ
አምባሳደር ብናልፍ ከፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሹመት ደብዳቤ እና የሥራ መመሪያ ተቀብለዋል
ፕሬዝዳንት ታዬ ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል
አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ተሸሙ።
በዛሬው እለት በብሄራዊ ቤተ መንግስት በተካሄደ ስነ ስርዓት ላይም አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሹመት ደብዳቤ እና የሥራ መመሪያ ተቀብለዋል።
በተጨማሪም አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት አማካኝነት ቃለ መሀላ መፈጸማቸውን ኢዝአ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዚህ ወቅት በሰጡት አስተያየት፣ ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የረጅም ዘመን ግንኙነትን የሚያጠናክር ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።
በተጨማሪም አሜሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባት ሀገር በመሆኗ በኢትዮጵያ ልማትና እድገት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አምባሳደሩ ጠንካራ ስራ ማከናወን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለጀመረችው የፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ውጤታማነት ከአሜሪካ ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በቀጣይ በሰላም፣ በጸጥታና በዳያስፖራ ጉዳዮች ዙሪያ ያቀደቻቸውን ግቦች ለማሳካት አምባሳደር ብናልፍ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም ባሳለፍነው ህዳር ወር ላይ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን መሾማቸው ይታወሳል።
አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም የሰላም ሚኒስትር በመሆን እንዲሁም ቀደማ ባሉት ጊዝያ በተለያዩ የመንግስት ኃላፊነቶች ላይ ለረጅም ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።