የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዛሬ ሪያድ ይገባሉ፤ ከሩሲያ ጋር ድርድር ለመጀመር ወይስ ...?
የአሜሪካ እና ሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሶስት አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ በሳኡዲ ይገናኛሉ
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/18/273-112237-54257127150-19deee2977-o_700x400.jpg)
ዜለንስኪ ኬቭ በማትሳተፍበት የአሜሪካ እና ሩሲያ ድርድር የሚደረስ ስምምነትን አንቀበልም ብለዋል
አሜሪካ እና ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት የተካረረ ግንኙነታቸውን ለማለዘብ ዛሬ የፊት ለፊት ውይይት ያደርጋሉ።
በሪያዱ ምክክር የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የመሩት ልኡክ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭና ከቭላድሚር ፑቲን አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ ጋር ይወያያል።
የሁለትዮሽ ምክክሩ የዋሽንግተን እና ሞስኮን ግንኙነት ማሻሻል በሚያስችሉ እና የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም በሚያግዙ ጉዳዮች ላይ እንሚያተኩር ክሬምሊን አስታውቋል።
ልኡካኑ በቅርቡ በሪያድ የሚገናኙት ትራምፕና ፑቲን በሚመክሩባቸው ነጥቦች ላይም እንደሚነጋገሩ ነው የተገለጸው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ እና የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ግን ዩክሬን ያልተሳተፈችበት የሰላም ንግግር የሶስት አመቱን ጦርነት አያስቆምም፤ ውጤቱም ተቀባይነት አይኖረውም እያሉ ነው።
ዜለንስኪ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኬቭ በሪያዱ የአሜሪካ እና ሩሲያ ድርድር ዙሪያ "የምታውቀው የላትም" ብለዋል። "ዩክሬን በራሷ ጉዳይ ባልተጋበዘችበት ድርድር የሚደረስ ስምምነትን አትቀበልም" ሲሉም አብራርተዋል።
አሜሪካ እና ሩሲያ ከሶስት አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ በሳኡዲ ምክክር በሚጀምሩበት በዛሬው እለት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ሪያድ ይገባሉ።
ጉብኝቱ ከድርድሩ ጋር ይያያዛል ወይ በሚል የተጠየቁት ዜለንስኪ "የሪያድ እና ሌሎች ሀገራት ጉብኝቴ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር ከመወሰኗ በፊት አስቀድሞ የተያዘ መርሃግብር ነው" በማለት ከዋሽንግተን እና ሞስኮ ንግግር ጋር እንደማይያያዝ ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንት ፑቲን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ዩሪ ኢሻኮቭም ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ለማደስ የሚደረገው የሪያድ ድርድር ሶስተኛ ወገንን (ዩክሬን) እንደማያካትት አረጋግጠዋል ብሏል አርቲ በዘገባው።
በምርጫ ቅስቀሳቸው "የዩክሬኑን ጦርነት በአንድ ቀን አስቆማለሁ" ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ተሳክቶላቸው ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት እንደገቡ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስልክ ደውለዋል፤ በቅርቡም በሳኡዲ ለመገናኘት መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ኬቭ በሞስኮ የተያዙባት ግዛቶችን መልሳ እንደማታገኝ እና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባልነት ጥያቄዋ እንዲቆም የሚሰጡት አስተያየት ዜለንስኪ እና የአውሮፓ መሪዎችን አስቆጥቷል።
ባለፈው ሳምንት በጀርመን ሙኒክ በተካሄደው የደህንነት ኮንፈረንስም የትራምፕ አስተዳደር በዩክሬኑ ጦርነት ዙሪያ የያዘው አቋም ዋነኛ መነጋገሪያ እንደነበር ይታወሳል።