እንግሊዝ የሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ዩክሬን ለመላክ መዘጋጀቷን አስታወቀች
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት አውሮፓውያን የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በሚደረገው ድርድር ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ ለማሳየት ነው ተብሏል

ፕሬዝደንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ከፑቲን ጋር በስልክ መናገራቸውን ይፋ ማድረጋቸውና ንግግር ይጀመራል ማለታቸው ዩክሬንንና አውሮፓውያን አጋሮቻቸውን አስደንግጧል
እንግሊዝ የሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ዩክሬን ለመላክ መዘጋጀቷን አስታወቀች።
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስተር ኪር ስትራመር ከጦርነት በኋላ ለሚኖር የሰላም ማስከበር ተሌእኮ ወታደሮች ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት አውሮፓውያን የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በሚደረገው ድርድር ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ ለማሳየት ነው ተብሏል።
የእንግሊዝን ሴትና ወንድ ወታደሮችን መጉዳት እንደማይፈልጉ የገለጹት ስትራመር ነገርግን በዩክሬን ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሩሲያውን ፕሬዝደንት ፑቲንን ማስቆም በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በትናንትናው እለት ዩክሬንና አውሮፓ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ትክክለኛ ንግግር እንደሚሳተፉና አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የምታደርገው ንግግር ፑቲን ስለሰላም ንግግሩ ምን ያህል ቁርጠኛ መሆናቸዉን ለማየት ነው ብለዋል።
ስትራመር ጦርነቱ የሚቆም ከሆነ ፑቲን ድጋሚ ጥቃት እንዲሰነዝሩ የሚፈቅድ መሆን የለበትም ማለታቸውን ሮይተርስ ዴይሊ ቴሌግራፍን ጠቅሶ ዘግቧል። ስትራመር የዩክሬን ሰላም አስከባሪዎችን ለመላክ እቅድ እንዳላቸው አስተያየት ሲሰጡ ይህ የመጀመሪያቸው ነው። ስትራመር ቀደም ሲል በዩክሬን የሰላም ስምምነት ላይ አስፈላጊ ሚና ለመጫወት ፈቃደኛ መሆኗን ገልጸው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስትራመር " አስፈላጊ ከሆነ ወታደሮቻችንን በማሰማራት" ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"ይህን ቀለል አድርጌ አላየውም" ያሉት ሰትራመር "የእንግሊዝ ወታደሮችን እስከማሰማራት የሚደርስ ኃላፊት ሊኖር እንደሚችል ይሰማኟል" ብለዋል።
ስትራመር የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በዩክሬን ጉዳይ በጠሩት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ይገኛሉ ተብለው ከሚጠበቁት መሪዎች ውስጥ ይገኙበታል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ከፑቲን ጋር በስልክ መናገራቸውን ይፋ ማድረጋቸውና ንግግር ይጀመራል ማለታቸው ዩክሬንንና አውሮፓውያን አጋሮቻቸውን አስደንግጧል። የትራምፕ የዩክሬን ልዩ መልእክተኛ ኬትዝ ኬሎግ ዩክሬንና ሌሎች አውሮፓውያን አጋሮች በንግግሩ እንደማይሳተፉ አስተያየት ሰጥተው ነበር።