አሜሪካ በሄሜቲ ወንድም አብደልራሂም ዳጋሎ ላይ ማዕቀብ ጣለች
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል ምክትል አዛዡ ንጹሃን እንዲገደሉና የሰብአዊ መብቶች እንዲረገጡ አድርገዋል በሚል ነው ማዕቀብ የተጣለባቸው
በአሜሪካ የሚገኙ በአብደል ራሂም ዳጋሎ ስም የተመዘገቡ ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል
አሜሪካ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) ምክትል አዛዥ አብደልራሂም ዳጋሎ ላይ ማዕቀብ ጣለች።
የመሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ወንድም በሰብአዊ መብት ጥሰት ነው በዋሽንግተን ማዕቀብ የተጣለበት።
በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛዋ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ቻድን ከሱዳን በሚያዋስነው ድንበር ላይ ጉብኝት ሲያደርጉ ነው በአብደልራሂም ዳጋሎ ላይ ማዕቀብ መጣሉን ይፋ ያደረጉት።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ተዋጊዎች ንጹሃንን በመግደል እና የወሲብ ትንኮሳ በማድረግ ወቀሳ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትም በንጹሃን ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ የሚቀርብበትን ወቀሳ ሲያስተባብል የቆየ ሲሆን፥ ጥፋተኞች ከተገኙ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ መግለጹን ሬውተርስ አስታውሷል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ግን ተጠያቂነትን ለማስፈን በጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ወንድም ላይ ማዕቀብ መጣሉ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ነው ያስታወቀው።
በአሜሪካ የሚገኙ በአብደል ራሂም ዳጋሎ ስም የተመዘገቡ ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸውንም ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው የአርኤስኤፍ የምዕራብ ዳርፉር አዛዡ ጀነራል አብዱል ራህማን ጁማ አሜሪካ እንዳይገቡ መታገዳቸውን ይፋ አድርገዋል።
ጀነራል ጁማ የሚመሩት ሃይል የምዕራብ ዳርፉር አስተዳዳሪ አርኤስኤፍን በተቃወሙ በስአታት ልዩነት ከነወንድማቸው እንደገደሏቸው ከታማኝ ምን አረጋግጠናል ነው ያሉት ብሊንከን።
አሜሪካ በሰኔ ወር 2023 ከሱዳን ጦር እና ከፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ጋር ግንኙነት ፈጥረው በጦርነት ትርፍ እያካበቱ ነው ባለቻቸው አራት ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
ዛሬ ማዕቀብብ የተጣለባቸው አብደልራሂም ዳጋሎ ንብረት የሆነው “አልጉናዴ” የተሰኘ የወርቅ አውጪ ኩባንያም ማዕቀብ ከተጣለባቸው ተቋማት መካከል አንዱ ነበር ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።