የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ግጭቱን በንግግር ለመፍታታ ፈቃደኛ መሆናቸውን ፕሬዝደንት ሩቶ አስታወቁ
ግጭቱን በቀጠናዊው ድርጅት ኢጋድ በኩል ለመፍታት የነበረው ጥረት እስካሁን ውጤታማ አልሆነም
ፕሬዝደንት ሩቶ አልቡርሃን እንደደወሉላቸው እና ኬንያ ገለልተኛ አይደለችም የሚለውን ወቀሳቸውን እንዳነሱላቸው ገልጸዋል
የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ግጭቱን በጠረንጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ንግግር ለመፍታት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ግጭቱን በቀጠናዊው ድርጅት ኢጋድ በኩል ለመፍታት የነበረው ጥረት እስካሁን ውጤታማ አልሆነም። ነገርግን አሁን ላይ ተፋላሚ ኃይሎቹ ግጭቱን በንግግር ለመፍታት ፈቃደኝነት ማሳየታቸውን ፕሬዝደንት ሩቶ ከአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ሩቶ አልቡርሃን እንደደወሉላቸው እና ኬንያ ገለልተኛ አይደለች የሚለውን ወቀሳቸውን እንዳነሱላቸው ገልጸዋል።
ሱዳን ቀደም ሲል ኬንያ በሱዳን ጉዳይ ስብሰባ ማድረጓን መቃወሟ ይታወሳል። የኢጋድ መሪዎች በአዲስ አበባ ባካሄዱት ስብሰባ የሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች እንዲገኙ ቢጋበዙም የሱዳን ጦር ተወካይ ሳይገኝ ቀርቷል።
መሪዎቹ ከስብሰባው በኋላ ባወጡት መግለጫ ግጭቱ በንግግር የማይፈታ ከሆነ ወታደራዊ ጣልቃገብነት እንደአማራጭ መያዛቸውን ገልጸው ነበር። ይህንን የመሪዎቹ ሀሳብ ሱዳን ሉአላዊነት የመጣስ ተግባር ነው ስትል ተቃውሞዋን ማሰማቷ ይታወሳል።
በሱዳን በአንድ ወቅት አጋር በሆኑት በሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አልቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ መካከል የተነሳው ግጭት ወራትን አስቶጥሯል።
አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ ሁለቱን ተፋላሚዎች በጂዳ ለማደራደር ያደረጉት ጥረትም ፍሬ አለባ ሆኗል።