የፌዴራል መንግስት እውቅና በነፈገው ክልላዊ ምርጫ ያሸነፈው ህወሓት ዛሬ አዲስ ክልላዊ መንግስት ይመሰርታል
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልላዊ ምርጫውን እንደተካሄደ አይቆጠርም ማለቱ የሚታወስ ነው
አዲስ የተመረጠው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔም በመቀሌ ተጀምሯል
ህወሓት ዛሬ አዲስ ክልላዊ መንግስት ይመሰርታል
በቅርቡ በተካሄደው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ ያሸነፈው ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) ዛሬ የክልሉን ካቢኔ በአዲስ መልክ እንደሚያዋቅርና መንግስት እንደሚመሰርት ይጠበቃል፡፡
አዲስ የተመረጠው የክልሉ ምክር ቤትም ይህንኑ ለማድረግ የሚያስችለውን 6ኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ጉባዔውን በመቀሌ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
ምክር ቤቱ በህወሓት የሚቀርብለትን የክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የዕጩ ካቢኔ አባላትን ሹመት እንደሚጸድቅም ይጠበቃል፡፡
ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ/ም የተካሄደው የትግራይ ክልል ምርጫ በፌዴራሉ መንግስት ህጋዊ አይደለም ተብሏል፡፡
እውቅና እንደሌለው እና እንደተካሄደ እንደማይቆጠር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
6ኛውን ሃገራዊ ምርጫ በተመለከተ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈውን የውሳኔ ሃሳብ አስመልክቶ ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫን የሰጡት የምክር ቤቱ አፈጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ምርጫው በትግራይ ክልል ጭምር ይካሄዳል ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡
ሆኖም ትናንት ምሽት በድምጸ ወያኔ በእንግድነት የቀረቡት የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ምርጫን በሚመለከት ከአምስት ዓመት በኋላ ነው የምንገናኘው ሲሉ ለአፈ ጉባዔው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡