የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን ሊጎበኙ ነው
ሩዋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ደቡብ አፍሪካ በአንቶኒ ብሊንከን የሚጎበኙ ሀገራት ናቸው
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከቀናት በፊት ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን መጎብኘታቸው ይታወሳል
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን ሊጎበኙ ነው
ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ነሀሴ ወር ላይ ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን እንደሚጎበኙ ኋይት ሃውስ አስታውቋል፡፡
ኋይት ኃውስ በድህረገጹ እንዳስታወቀው የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ኪጋሊ፣ ኬንሺያሳ እና ፕሪቶሪያ በማቅናት ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡
ከአንቶኒ ብሊንከን ባለፈም በተመድ የአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ በነሀሴ ወር ላይ ወደ ዩጋንዳ እና ጋና እንደሚያቀኑ ዘገባው አክሏል።የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር ኬንያን እና ሶማሊያን ከቀናት በፊት መጎብኘታቸው ይታወሳል።
የብሊንከን ጉብኝት ከቀናት በፊት ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን ከጎበኙት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጊ ላቭሮቭ ጋር ይገናኝ አይገናኝ የታወቀ ነገር የለም።
ሰርጌ ላቭሮቭ በአፍሪካ ጉብኝታቸው በዓለም ላይ እየተከሰተ ላለው የምግብ እና ነዳጅ መወደድ ምዕራባውያን እየጣሉት ያለው ማዕቀብ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።
አሜሪካ እና ምዕራባውያን ሀገራት በበኩላቸው ለዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ መናር ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ በመፈጸሟ የመጣ እንደሆነ በመናገር ላይ ናቸው።
ሁለቱ ሀያላን ሀገራት ማለትም አሜሪካ እና ሩሲያ ከአፍሪካ አጋር ሀገራትን ለማግኘት ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን ወደ አፍሪካ በማድረግ ላይ ናቸው።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባሳለፍነው ሳምንት ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን ጎብኝተው ወደ ፓሪስ የተመለሱ ሲሆን የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በዩክሬን ጉዳይ ያሳዩትን አቋም ተችተዋል።
aXA6IDMuMTI5LjE5LjI1MSA=
ejasoft island