ዩክሬን በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ዜጎች አገልግሎት መስጠት አቆመች
ሀገሪቱ አገልግሎቱን ያቋረጠችው እድሜያቸው ለብሔራዊ ውትድርና የደረሱ ዜጎች ወደ ሀገሯ እንዲመጡ ለማድረግ ነው
በአውሮፓ ሀገራት ከሚኖሩ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዩክሬናዊያን መካከል 860 ሺህ ያህሉ ከ18 ዓመት በላይ ናቸው ተብሏል
ዩክሬን በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ዜጎች አገልግሎት መስጠት አቆመች።
ለአንድ ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል።
ይህ ጦርነት በድርድር እንዲቆም የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም እስካሁን መልኩን እየቀያየረ እስካሁን ቀጥሏል።
ዩክሬን ባንድ በኩል የጦር መሳሪያዎችን ከተለያዩ ሀገራት በማሰባሰብ ላይ ስትሆን በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ ወታደራዊ ግዳጅ በዜጎቿ ላይ ጥላለች።
ሀገሪቱ ከሩሲያ ጋር ለሚደረገው ጦርነት እድሜያቸው ከ18-60 ዓመት የሆናቸው ዜጎች ወታደራዊ ተቋሟን እንዲቀላቀሉ ግዳጅ ጥላለች።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዩክሬናዊያን ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት እንደተሰደዱ ተገልጿል።
ይሁንና ዩክሬን የወታደር እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ በውጭ ሀገራት ያሉ ዜጎቿ እንዲመለሱ እና ሀገራቸውን ከሩሲያ ጥቃት እንዲጠብቁ ጥሪ አድርጋለች።
ይሁንና እነዚህ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዩክሬናዊያን ወደ ሀገራቸው በግዴታ እንዲመለሱ ፓስፖርት እና መሰል አገልግሎቶችን በውጭ ሀገራት ባሉ ኢምባሲዎች ውና ኮንሱላ ጽህፈት ቤቶች እንዳያገኙ እገዳ ጥላለች።
ዩክሬን በውጭ ሀገራት ተሰደው ካሉ ዜጎቿ መካከል 860 ዩክሬናዊያን እድሜያቸው 18 እና ከዛ በላይ ይሆናል ተብሏል።
እድሜያቸው የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት እንዲቀላቀሉ የሚፈቅድላቸው እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዩክሬናዊያን ወደ ኪቭ ካልተመለሱ ማንኛውም የዜግነት አገልግሎት እንዳይሰጣቸው እገዳ እንደተጣለባቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ በዚህ እንዳለ ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን በኩል ድል እየቀናት እና ቦታዎችን ከዩክሬን ጦር እየተረከበች መሆኗ ተገልጿል።
የአሜሪካ ህግ አውጭ ምክር ቤት ዩክሬንን ጨምሮ ለእስራኤል እና ታይዋን ከ60 ቢሊዮን በላይ ዶላር እርዳታ እንዲሰጥ ውሳኔ አሳልፏል።