አሜሪካ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ላከች
ፔንታጎን ከ2 እስከ 3 ሺህ የሚገመቱ ወታደሮችን የላከው ከሄዝቦላህ ጋር ጦርነት ለጀመረችው እስራኤል ድጋፍ ለማድረግ ነው
አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ 43 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች አሰማርታለች
አሜሪካ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተጨማሪ ወታደሮችን መላኳን አስታወቀች።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ምን ያህል ወታደሮችን ወደ ቀጠናው እንደላከ ባይገልጽም ኒውዮርክ ታይምስ ከ2 ሺህ እስከ 3 ሺህ እንደሚደርሱ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
በትናንትናው እለት ወደ መካከለኛው ምስራቅ የተላኩት የአሜሪካ ወታደሮች በቀጠናው የተሰማሩ የሀገሪቱን ወታደሮች ቁጥር 43 ሺህ አድርሶታል።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሳብሪና ሲንግ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከወታደሮቹ ጋር በርካታ የውጊያ ጄቶችም ተልከዋል።
የተላኩት “ኤፍ-15ኢ”፣ “ኤፍ- 16” እና “ኤፍ-22” ጄቶችና “ኤ-10” የውጊያ አውሮፕላኖች በቀጠናው የአሜሪካን የአየር ሃይል ዝግጁነት ያጠናክሩታል ነው ያሉት ቃል አቀባዩዋ።
አሜሪካ ተጨማሪ ወታደሮችና የጦር መሳሪያዎችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ የላከችው ከሄዝቦላህ ጋር ጦርነት የጀመረችው አጋሯ እስራኤል ድጋፍ የምትሻ ከሆነ ለማገዝ መሆኑን አስታውቃለች።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች በኋላ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች እና የውጊያ አውሮፕላኖችን በብዛት ወደ ቀጠናው የላከችው ዋሽንግተን የኢራንን ተጽዕኖ ለመግታት በሚል የተለያዩ እርምጃዎች ወስዳለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫም በቀጠናው የተሰማራችውና በአብርሃም ሊንከስ ስም የተሰየመችው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ቆይታ በአንድ ወር እንዲራዘም መወሰኑን መግለጻቸውን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
ሁለተኛዋ የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ መርከብ “ዩኤስኤስ ሃሪ ኤስ ትሩማን”ም ከቨርጅኒያ ተነስታ ወደ አውሮፓ እየቀዘፈች ነው የተባለ ሲሆን፥ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር በመጓዝ በእስራኤል ላይ ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን በመከላከል ላይ እንደምትሰማራ ተገልጿል።
በተያያዘ ዜና እግረኛ ጦሯን ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ ያስገባችው እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር ከባድ ውጊያ እያካሄደች መሆኑ ተዘግቧል። ሄዝቦላህም ወደ እስራኤል ሮኬቶችን እያስወነጨፈ ይገኛል።
ቴል አቪቭን ለማገዝ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ የላከችው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም እስራኤልና ሄዝቦላህ በአፋጣኝ ተኩስ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።