በዩክሬን የሚገኙ ኤምባሲዎቻቸውን የዘጉ ምዕራባውያን ሀገራት
ሀገራቱ ኤምባሲዎቻቸውን የዘጉት ሰሞናዊ ውጥረትን ተከትሎ የሩስያን የአየር ጥቃት ፍራቻ ነው
የሩስያው ፕሬዝዳንት አዲስ ባጸደቁት የኒዩክሌር ዶክትሪን ምዕራባውያን በቀጥታ ከሩስያ ጋር እየተዋጉ ነው ብለዋል
በዩክሬን ዋና ከተማ የተጠናከረውን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ረቡዕ ጠዋት በኪቭ የሚገኘውን ኤምባሲ ዘግታለች፡፡
ዋሽንግተን በኤምባሲው ላይ ከፍተኛ የአየር ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል አገኝሁት ባለችው የደህንነት መረጃ ነው ውሳኔውን ያሳለፈችው፡፡
የጆ ባይደን አስተዳደር ዩክሬን አሜሪካን ሰራሽ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን በሩስያ ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎችን ለማጥቃት ፈቃድ ከሰጡ በኋላ የአካባቢው ውጥረት ተባብሷል፡፡
አዲስ ባጸደቁት የኒዩክሌር ዶክትሪን ሀገራት የኔቶ አባል ባይሆኑም በአባላቱ ድጋፍ የሚደረግላቸው ከሆነ ጥምር ጥቃት እንደሰነዘሩ ይቆጠራል ያሉት የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ ለሚሰነዘርባት ጥቃት ተመጣጣኝ ያለችውን ጥቃት እንደምትሰነዝር ዝተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ስጋት የገባቸው የምዕራባውያን ሀገራት በኪቭ የሚገኙ ኤምባሲዎቻቸውን እየዘጉ ይገኛሉ፡፡
በዚህም ከአሜሪካ በተጨማሪ እስካሁን ጣሊያን እና ግሪክ ኤምባሲዎቻቸውን የዘጉ ሲሆን ፈረንሳይ የኤምባሲው ሰራተኞች ልዩ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስባለች፡፡
ከባይደን በተሰጣት የረጅም ርቀት ሚሳኤል ፈቃድ በሩስያ የጦር መሳርያ ማከማቻ ላይ የመጀመርያውን ጥቃት የፈጸመችው ዩክሬን በአጸፋው የተጠናከረውን የሞስኮ የአየር ጥቃት ጉዳት ለመቀነስ ዜጎች የቦምብ መጠለያዎች ውስጥ እንዲቆዩ አሳስባለች፡፡
ዩክሬን ወደ ሩሲያ ግዛት በምዕራቡ ዓለም በተደገፉ ሚሳኤሎች እንድትመታ ፍቃድ ካገኝች እንደ ትልቅ የደህንነት ስጋት እንደምትወስድ ሩሲያ ለአሜሪካ እና አጋሮቿ ለሳምንታት ስታሳስብ ቆይታለች።
የሩስያ የውጭ ደህንነት ሃላፊ ሰርጌይ ናሪሽኪን በዛሬው እለት ታትሞ በወጣ የሩስያ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሞስኮን ለማጥቃት የሚውሉ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን ለማንቀሳቀስ በሰው ሀይል እና በሌሎች መንገዶች በሚደግፉ የኔቶ አባል ሀገራት ላይ ጥቃት ትፈጽማለች ብለዋል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው ሞስኮ በዩክሬን ዋና ከተማ የህዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶች ላይ አነጣጥራ ባጠናከረችው ጥቃት ኤምባሲዎቻቸውን ያልዘጉ ሀገራት የሀይል እና የውሀ መሰረተ ልማት ሊቋረጥ ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡
የአየር ጥቃቱ አሁን በሚገኝበት አደገኛነት ከቀጠለም ተጨማሪ ሀገራት ኤምባሲዎቻቸውን ሊዘጉ እና ሰራተኞቻቸውን ሊያስወጡ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡