ደቡብ ኮሪያ በፓሪስ ኦሎምፒክ ለሰሜን ኮሪያ አትሌቶች የተሰጠው ዘመናዊ ስልክ እንዲነጠቅ ጠየቀች
የሴኡል ባለስልጣናት የስልክ ስጦታው ተመድ በሰሜን ኮሪያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ይተላለፋል ብለዋል
በዘንድሮው አሎምፒክ ለሚሳተፉ ሁሉም አትሌቶች ዘመናዊ ስልክ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል
የደቡብ ኮርያ ባለስልጣናት ለሰሜን ኮርያ አትሌቶች የተሰጠው ዘመናዊ ሳምሳንግ ጋላክሲ ስልክ እንዲነጠቅ ጠይቀዋል፡፡
የስልክ ስጦታው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኒውክሌር ጦር መሳርያ ፕሮግራሟ ምክንያት በሰሜን ኮርያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ይተላለፋል ብለዋል ባለስልጣናቱ፡፡
የዘንድሮው ኦሎምፒክ ዋነኛ አጋር ከሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ግዙፉ የደቡብ ኮርያ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሳምሳንግ ለሁሉም ተሳታፊ አትሌቶች አዲስ ምርት የሆነውን የሳምሳንግ ጋላክሲ ዜድ ተጣጣፊ የሞባይል ስልክ በስጦታ መልክ አበርክቷል፡፡
የሞባይል ስልክ ስጦታው ለሁሉም አትሌቶች መሰጠቱን ያረጋገጠው አለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ ከሰሜን ኮርያ አትሌቶች ስልኮቹን እንዲነጥቅ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
የደቡብ ኮርያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በ2017 የጸጥታው ምክር ቤት በፒዮንግያንግ ላይ ማዕቀብ ባሳለፈበት የውሳኔ ሀሳብ 2397 መሰረት ስማርት ስልኮች ለሰሜን ኮርያ እንዳይገቡ፣ እንዳይሸጡም ሆነ በስጦታ መልክ እንዳይሰጡ ይከለክላል ብሏል፡፡
የውሳኔ ሀሳቡ በዜጎች እና በመንግስት መካከል ያለውን የማዕቀብ አፈጻጸም ልዩነት አላስቀመጠም ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አትሌቶቹ ስልኮቹን ይዘው ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ መፈቀድ የለበትም ሲል ቅሬታውን አቅርቧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚቴስትሩ ቃል አቀባይ ሊ ጅዎንግ ማዕቀቡ ከትናንሽ ቁሶች እስከትላልቅ የኢንዱስትሪ ማሽኖች በግልጽ ያስመጣቸው ክለከላዎች እንዳሉ ገልጸው መንግስታቸው ክልከላው በተገቢው መንገድ እንዲፈጸም ቀዳሚ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
በ2018 በደቡብ ኮርያ አዘጋጅነት በተካሄደው የክረምት ኦሎምፒክ ተመሳሳይ የሞባይል ስልክ ስጦታ ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ ተሳታፊ የነበሩት ሰሜን ኮሪያውያን ከሌሎች ሀገራት በተለየ የሚሰጣቸውን ስልክ ወደ ሀገራቸው ከመሄዳቸው በፊት መመለስ እንደሚኖርባቸው ሲነገራቸው ስጦታውን አንቀበልም ብለው ነበር፡፡
በዘንድሮው የፓሪሱ ኦሎምፒክ ሰሜን ኮርያ በ16 አትሌቶች በጠረጴዛ ቴንስ ፣ ዋና ፣ ነጻ ትግል እና ቦክስን ጨምሮ በ7 አይነት ውድድሮች በመሳተፍ ላይ ትገኛለች፡፡
በ2021 በቶኪዮ በተደረገው የበጋ ኦሎምፒክ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ የእንቅስቃሴ እቀባ አድርጋ የነበረችው ፒዮንግያንግ በመድረኩ አልተሳተፈችም፡፡
አለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴም በቶኪዮው ኦሎምፒክ አትሌቶችን አላክሽም በሚል በ2022 የቤጂንግ የክረምት ኦሎምፒክ ላይ እንዳትሳተፍ ቅጣት አስተላልፎባት እንደነበር ይታወሳል፡፡