ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ ሶስት የስለላ ሳተላይቶችን ልታመጥቅ ነው
በኮሪያ ልሳነ ምድር በየትኛውም ጊዜ ጦርነት ሊከፈት እንደሚችል የገለጸችው ፒዮንግያንግ፥ ጦሯ በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ አሳስባለች
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ወር ያመጠቀቻት የስለላ ሳተላይት የሴኡልና የዋሽንግተንን እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ምስሎችን እየላከች ነው ተብሏል
ሰሜን ኮሪያ በነገው እለት በሚገባው የፈረንጆቹ አዲስ አመት 2024 ተጨማሪ ሶስት የስለላ ሳተላይቶችን እንደምታመጥ አስታውቃለች።
ሳተላይቶቹ ሀገሪቱ ጠላቶቼ ብላ የፈረጀቻቸውን ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመከታተል መረጃ እንደሚያቀብሏትም ነው የተገለጸው።
ፒዮንግያንግ ባለፈው ወር ያመጠቀቻት የስለላ ሳተላይት የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያን ወታደራዊ ጣቢያዎች ምስል በማንሳት መላኳ መገለጹ የሚታወስ ነው።
በ2024 ተጨማሪ ሳተላይቶችን የማምጠቅ ሙከራው ከተሳካም ወታደራዊ ዝግጁነቷን ይበልጥ እንደሚያጎለብቱላት ነው የሚጠበቀው።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በገዥው ሰራተኞች ፓርቲ የበጀት አመት ማጠናቀቂያ ስብሰባ ወቅት ባደረጉት ንግግር ከጎረቤታቸው ደቡብ ኮሪያ ጋር የመዋሃድ እድሉ በረጅም አመታት ውስጥ የሚሳካ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ስለሁለቱ ኮሪያዎች የውህደት ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሱት ኪም ጆንግ ኡን፥ ሴኡል እንደጠላት ስለፈረጀችን የኒዩክሌር ልማታችን ከማጠናከር ውጭ አማራጭ አላገኝንም ማለታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ወር የስለላ ሳተላይት ስታመጥ ከሴኡል ጋር ወታደራዊ ውጥረቱን ለማርገብ ደርሳው የነበረውን ስምምነት እስከማፈረስ መድረሷም የሚታወስ ነው።
በ2023 ተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራዎችን ያደረገችው ፒዮንግያንግ በቅርቡም አሜሪካን ሊመታ የሚችል አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል (ሃውሶንግ 18) ማስወንጨፏም አሜሪካና ደቡብ ኮሪያን አስቆጥቷል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ግን ሀገራቸው የኒዩክሌር ልማቷን እንድትገፋበት ያደረገው የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ “ሰሜን ኮሪያን የመውረር ፍላጎት” መሆኑን ያነሳሉ።
“ጠላቶቻችን እኛን ለመውረር ሃላፊነት የጎደለው አካሄድን መርጠዋል፤ በኮሪያ ልሳነ ምድር በየትኛውም ጊዜ ጦርነት መነሳቱ አይቀርም” ነው ያሉት ኪም።
ደቡብ ኮሪያ የአሜሪካ የኒዩክሌር መሳሪያ ማከማቻ ማዕከል ሆናለች ሲሉ በመውቀስም የሀገራቱ እንቅስቃሴ “የአለም ጦርነት መነሳቱ እንደማይቀር የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል።
ኪም ባለፈው ሳምንትም ለዚህ ስጋት የሚመጥን ኒዩክሌርን ጨምሮ በቂ ወታደራዊ ዝግጅት እንዲደረግ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
የሰሜን ኮሪያን የስለላ ሳተላይት ማምጠቅም ሆነ የሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፍ አጥብቀው የሚያወግዙት ዋሽንግተን እና ሴኡልም ወታደራዊ ትብብራቸውን ማጠናከራቸውን ቀጥለዋል።