ልዩ መልእክተኛው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡና በግጭቱ ዙሪያ ከመንግስት ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ጄፈሪ ፌልትማን ጅቡቲ መግባታቸውን የኢጋድ ዋና ጽኃፊ ወርቅነህ ገበየሁ ገልጸዋል፡፡
ዋና ጸኃፊው ወርቅነህ በጅቡቲው የኢጋድ ቢሯቸው ፍልትማንን መቀበላቸውንና በቀጣናዊ የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ጽፈዋል፡፡ኢጋድና አሜሪካ በተለያዩ መስኮች ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው የተናሩት ዋና ጽኃፊው በሰላም፣ መረጋጋትና በልማት ዙሪያ ትብብራቸውን ለማጠናከር ይሰራሉ ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ሶስት ቀናት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።
በአሁን ሰአት ጂቡቲ የሚገኙት ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ከኢትዮጵያእና በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጉብኝት እንደሚያደርጉም ተገልጿል።
ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በሶስቱ ሀገራት ለዘጠኝ ቀናት ያክል በሚያደርጉት ቆይታም ከሀገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ተጠቅሷል።ውይይቱም በአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልጽግናን ማምጣት በሚያስችሉ ዕድሎች የተመለከተ እንደሚሆንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ከዚህ ቀደምም በግንቦት ወር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በግብፅ፣በኤርትራ እና በሱዳን ጉብኝት አድርገው እንደነበረ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው የነበረ ሲሆን፤ በህዳሴ ግድብ፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገውም ነበረ።
አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማንን ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ላይ መሾሟ ይታወሳል።
አዲሱ የኃላፊነት ስፍራ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተፈጠረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል ያለውን አለመግባባት በቅርበት ለመከታተል ያለመ ነው።