የአማራ ክልል መንግስት ህወሃት ወልዲያ ላይ በተኮሰው ከባድ መሳሪያ በንጹሀን ላይ ጉዳት ማድረሱን ገለጸ
የክልሉ መንግስት በህወሃት ኃይሎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል
የህወሃት ኃይሎች በአማራ ክልል ላይ ባደረሱት ጥቃት ታሪካዊቷን ላሊበላ ከተማን ጨምሮ ሌሎች የሰሜን ወሎ ቦታዎችን መያዛቸውን ገልጸዋል
የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለአል ዐይን ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ የህወሀት ታጣቂዎች በወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ከባድ መሳሪያ መተኮሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት በአማራ ክልል የሠሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ዋና ከተማ በሆነችው የወልድያ ከተማ ከማታ ጀምሮ እስከ ዛሬ አራት ሰዓት ድረስ ከፍተኛ ውጊያ ሲደረግ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ቡድኑ ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ወደ ወልድያ ከተማ ተኮሷዋል ባሏቸው ከባድ መሳሪዎችም በንጹኃን ላይ ጉዳት መድረሱን አቶ ግዛቸው ገልጸዋል፡፡ ትናንትና ምሽት ላይ ህወሃት የተኮሳቸው ከባድ መሳሪዎች ወልድያ ከተማ በሚገኘው ሼክ ሁሴን መሐመድ አሊ አላሙዲን ስታዲዬም እና በሕዝብ መኖሪያ ቤቶች ላይ ማረፉንም አቶ ግዛቸው ተናግረዋል፡፡
ዛሬም ጭምር ተከፍቶ በነበረው ተኩስ በርካታ ጉዳት መድረሱን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ግን የተወሰነ የተኩስ ፋታ መኖሩን ለአል ዐይን ኒውስ ተናግረዋል፡፡
ወደ ወልዲያ ከተማ በተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች የደረሰው ዝርዝር ጉዳት እስካሁን ባለው ሁኔታ ባይገለጽም በንጹሃን ላይ ግን ጉዳት መድረሱን አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ተናግረዋል፡፡ ህወሃት አሁን ላይ ይዟቸዋል ከተባሉት የአማራ ክልል አካባቢዎች ማስወጣት እንደ አንድ ተግባር ቢያዝም መንግስት ግን ቡድኑን እስከመጨረሻ ለማጥፋት “ቁርጠኛ” መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ለይ የህወሃት ኃይል በሶስት አቅጣጫ ማለትም በባህር ዳር መውጫ፤ በሀራ እና በመርሳ በኩል ተኩስ ቢከፍትም የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ የቡድኑ ተዋጊዎች መገደላቸውን አቶ ግዛቸው አስታውቀዋል፡፡ አሁንም በተወሰኑ ቦታዎች የቀሩ የህወሃት ታጣቂዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ ስራው እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የወልዲያ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት፤ በበኩሉ ነሀሴ ሁለት እና ሶስት ቀን 2013 ዓ.ም ከከተማዋ ቅርብ ርቀት ላይ በተደጋጋሚ ከባድ መሣሪያ መወርወሩን ገልጿል፡፡
የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች የፌዴራል መንግስት በህዋሀት ቡድን ላይ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ ቡድኑ ”ከተማዋን ለማውደም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ከባድ መሣሪያ መወርወር ጀምሯል” ማለታቸውን የከተማዋ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ብለዋል።
የፌደራል መንግስት፤ በትግራይ ክልል ግጭቱ ከተጀመረ ከ8 ወራት በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ቢያወጣም ግጭቱ ሊቆም አልቻለም፡፡ ግጭቱ ወደ አማራና አፋር ክልል በመስፋፋት ከ300ሺ በላይ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት መሆኑን መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ህወሃት በአማራ ክልል ላይ ባደደረሰው ጥቃት ታሪካዊቷን ላሊበላ ከተማን ጨምሮ ሌሎች የሰሜን ወሎ ቦታዎችን መያዙ ተዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፤ ቡድናቸው በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን እና በዚህም እስካሁን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት አለማድረሳቸውን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ከወራት በፊትየፌደራል መንግስት፣ ህወሃት ሀገረመንግስቱን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ላይ ተሳትፏል በሚል በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት እንዲፈረጅ አድርጓል፡፡