አሜሪካ የተመድ ዋና ጸሃፊን ትሰልል እንደነበር አፈትልኮ የወጣ ሚስጥራዊ ሰነድ አመለከተ
ዋሽንግተን ጉቴሬዝ የሩሲያን ፍላጎት ያስጠብቃሉ ብላ እንደምታምን ነው ሰነዱ ያሳየው

አፈትልከው የወጡት የአሜሪካ ሰነዶች አሁንም መነጋገሪያነታቸው ቀጥሏል
አሜሪካ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ትሰልል እንደነበረ አፈትልኮ የወጣ ሚስጥራዊ ሰነድ አመለከተ።
የአሜሪካ መንግሰት ጉቴሬዝ የሩሲያን ፍላጎት ለማሟላት ፍላጎት አላቸው ብሎ እንደሚያምን ሰነዱ ጠቁሟል።
ከሩሲያ ጋር በጥቁር ባህር በኩል የዩክሬን ስንዴን ለአለም ገበያ ለማቅረብ ስምምነት ሲደረስ የመንግስታቱ ድርጅት እና ቱርክ አደራዳሪ እንደነበሩ ይታወሳል።
ጉቴሬዝ ይህ ስምምነት ሲደረስ ሃላፊነታቸውን ዘንግተው የሞስኮን ጥቅም ለማስከበር ጥረት አድርገዋል ይላል አንደኛው ሰነድ።
ይህም የቭላድሚር ፑቲንን ሀገር በዩክሬን ለፈጸመችው በደል ተጠያቂ እንዳትሆን ያደርጋል በሚልም በአድልኦ ይከሳቸዋል።
ሰነዱ ዋሽንግን አንቶኒዮ ጉቴሬዝን በቅርበት ክትትል እንደምታደርግባቸው ያመላከተ ነው።
በዋና ጸሃፊው እና በምክትላቸው መካከል የነበሩ ንግግሮች እና የመረጃ ልውውጦችንም አካቷል።
ሚስጢራዊ ናቸው ተብለው ስለተለቀቁት ሰነዶች የመንግስታቱ ድርጅት ምላሽ መስጠት አልፈልግም ማለቱን ሬውተርስ አስነብቧል።
ይሁን እንጂ ጉቴሬዝ በሞስኮ ላይ ተለሳልሰዋል በሚል የሚነሳውን ክስ አጠጥሎታል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ሩሲያ እና ዩክሬን ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የጣሩት የአለም የምግብ ዋጋ ንረት እንዲቀንስና የማዳበሪያ አቅርቦቱ እንዲያድግ እንጂ ለሞስኮ የተለየ ጥቅምን ለማስገኘት አለመሆኑንም ድርጅቱ መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከአሜሪካ አፈትልከው ወጡ የተባሉት ሚስጢራዊ ሰነዶች ከዋሽንግተን እስከ ኬቭ፤ ከቴል አቪቭ እስከ ሴኡል መነጋገሪያ ሆነው ሰንብተዋል።
አሜሪካ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተዘዋወሩ የሚገኙ እጅግ ሚስጢራዊ የሆኑ ሰነዶች በማንና እንዴት እንደወጡ ይጣሩ ዘንድ ማዘዟ ተገልጿል።
ዋይትሃውስ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት (ፔንታጎን) ጉዳዩን እንዲያጣራ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፔንታጎን በበኩሉ አፈትልከው ወጡ የተባሉትን ሰነዶች፣ ካርታዎች እና ፎቶግራፎች ትክክለኛነት እየመረመረ መሆኑን ትናንት ይፋ አድርጓል።