ሩሲያ ስንዴዋን ለድሃ የአፍሪካ ሀገራት በነጻ ልትሰጥ እንደሆነ ተገለጸ
ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን የነጻ ስንዴውን ከሚያገኙ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል
የሩሲያ እና ቱርክ ፕሬዝዳንቶች ለድሃ ሀገራት ስንዴ በነጻ ለማጓጓዝ መስማማታቸው ተገልጿል
ሩሲያ ስንዴዋን ለድሃ የአፍሪካ ሀገራት በነጻ ልትሰጥ እንደሆነ ተገለጸ።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ስምንት ወራት ያለፈው ሲሆን በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ መናርን ያመጣ ሲሆን፤ ምግብ እና ነዳጅ ከውጭ ሀገራት የሚያስገቡ ሀገራትን ደግሞ የበለጠ ለአደጋ አጋልጧል።
የዩክሬን እና ሩሲያ የውጭ ንግድ ዋነኛ መስመር የሆነው ጥቁር ባህር በጦርነቱ ምክንያት አገልግሎት አቋርጦ የነበረ ሲሆን በተመድ እና ቱርክ አሸማጋይነት የሕ የንግድ መስመር ወደ አገልግሎት ተመልሷል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ኤርዶሃን ከሩሲያ አቻቸው ቭለድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ሩሲያ በነጻ ስንዴዋን ወደ ድሃ ሀገራት ለማጓጓዝ መስማማቷ ተገልጿል።
የሩሲያን ስንዴ በነጻ ከሚሰጣቸው ሀገራት መካከልም ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን የተጠቀሱ ሲሆን ሀገራቱ የምግብ ችግር እንዳለባቸውም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
በተመድ እና ቱርክ አደራዳሪነት በጥቁር ባህር የጉዞ እና የንግድ መስመር ላይ ከ10 ሚሊዮን በላይ ቶን ስንዴ መጓጓዙ ተገልጿል።
ዩክሬን በፈረንጆቹ 2014 ላይ በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ በተቀላቀለችው ክሪሚያ ላይ የድሮን ጥቃት አድርሳለች በሚል ሩሲያ ከጥቁር ባህር ትራንሰፖርት ስምምነት መውጣቷን ተናግራ ነበር።
ይሁንና ዳግም በተደረገ ድርድር ዩክሬን በጥቁር ባህር ላይ ጥቃት እንደማትከፍት የጽሁፍ ማረጋገጫ መስጠቷን ተከትሎ ሩሲያ ወደ ስምምነቱ ዳግም መመለሷን አስታውቃለች።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዚህ በፊት ሞስኮ የአፈር ማዳበሪያ ምርቶቿን ለአፍሪካ ሀገራት በነጻ እንደምታጓጉዝ መናገራቸው ይታወሳል።