ሩሲያ በአውሮፓ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ካምፖች ላይ ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል ነገረ
አሜሪካ ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን እንድትጠቀም የምትፈቅድ ከሆነ ሞስኮ ጥቃት ልታደርስ ትችላለች ተብሏል
በኒውዮርክ የሚገኙት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ከአሜሪካው አቻቸው ጋር በሚሳይል አጠቃቀም ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል
ሩሲያ በአውሮፓ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ካምፖች ላይ ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል ነገረ።
አሜሪካ ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎችን ለማጥቃት ፈቃድ የምትሰጥ ከሆነ ሞስኮ በአውሮፓ በሚገኙ የአሜሪካ ካምፖች ላይ ድብቅ ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል ተነግሯል፡፡
የዋሽንግተን የደህንነት መስሪያ ቤቶች ያወጡትን መረጃ ጠቅሶ ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ሞስኮ በቀጠናው በሚገኙ አጋሮች እና በአሜሪካ የጦር ካምፖች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት እያደረገች ነው፡፡
የደህንነት እና ስለላ ተቋማቱ እንዳሉት ሩሲያ ግጭቱ ቀጠናዊ መልክ እንዲይዝ ስለማትፈልግ ቀጥተኛ ጥቃት ባትሰነዝርም በአካባቢው የሚገኙ ካምፖችን እንቅስቃሴ የሚገድቡ የተለያዩ የድብቅ ጥቃቶችን ልትፈጽም ትችላለች ብለዋል፡፡
በዚህም ድንገተኛ አደጋዎችን ማድረስ ፣ የእስት ቃጠሎ እና የመሰረተ ልማቶችን በድብቅ ማውደም እንዲሁም ሌሎች ለማስተባበል የሚመቹ የተለያዩ ጥቃቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ ነው የተባለው፡፡
ምንም እንኳን ዩክሬን በምዕራቡ ዓለም የሚቀርቡ ሚሳይሎችን በነጻነት እንድትጠቀም ቢፈቀድላትም ከቁጥራቸው ውስንነት የተነሳ በግጭቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አያመጣም።
በተጨማሪም ከመጀመሪያዎቹ ጥቃቶች በኋላ ሩሲያ ጠቃሚ ወታደራዊ ኢላማዎችን ከጥቃት ክልል ውጭ በማዛወር የኪቭን ማንኛውንም ወታደራዊ ዓላማ መሳካት ከባድ እንደሚያደርገው ነው የተገለጸው፡፡
ከዚህ ይልቅ ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን እንድትጠቀም መፍቀድ በዓለም ዙሪያ በአሜሪካ ወታደራዊ ንብረቶች እና ካምፖች ላይ አደገኛ ጥቃትን ሊያስከትል የሚችል ከፍተኛ ቁማር ነው ሲሉ የደህንነት ተቋማቱ አስጠንቅቀዋል፡፡
አሜሪካ እና አጋሮቿ ለዩክሬን ሶስት አይነት የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች አቅርበዋል። እነርሱም አሜሪካን ሰራሹ (ATACMS) ፣ የብሪታንያው ስቶርም ሻዶ እንዲሁም የፈረንሳዩ ስካልፕ ናቸው፡፡
ኪቭ እነዚህን ሚሳይሎች በክሪሚያ እና በሌሎች ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ተጠቅማባቸዋለች፡፡
ሆኖም በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎችን ለመጠቀም ምዕራባውያን እንዲፈቅዱላት ተደጋጋሚ ጥያቄዋን እያቀረበች ትገኛለች፡፡
ምዕራባውያን ይህን ፈቃድ የሚሰጡ ከሆነ የሞስኮን ቀይ መስመር መተላለፍ ነው ያሉት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ውሳኔው አሜሪካ እና ኔቶ በጦርነቱ በቀጥታ እንደተሳተፉ የሚያስቆጥር ነው ብለዋል፡፡