የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 400 ሚሊየን ዋጋ ያላቸው ቴስላ ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ይዞት የነበረውን እቅድ ሰረዘ
ሚኒስቴሩ ከቴስላ ኩባንያ ብቻ ሊፈጽመው የነበረውን እቅድ በመቀየር ሌሎች መኪና አምራቾች ግዢው ላይ እንዲሳተፉ ፈቅዷል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/14/273-114138-whatsapp-image-2025-02-13-at-4.35.54-pm_700x400.jpeg)
በአዲሱ የትራምፕ አስተዳደር የቴስላ ኩባንያ ባለቤት ኢለን መስክ ተጽዕኖ እያየለ እንደሚገኝ እየተነገረ ነው
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስርያቤት ከቴስላ ኩባንያ 400 ሚሊየን ዋጋ ያላቸው ጥይት የማይበሳቸው ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ይዞት የነበረውን እቅድ መሰረዙን አስታውቋል፡፡
መስሪያቤቱ ከቴስላ ኩባንያ ጋር ብቻ ለአምስት አመት የሚቆይ የተሸከርካሪ ግብይት ለመፈጸም የግብይት እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም በተሻሻለው የግዢ ሰነድ የቴስላን ስም አውጥቷል፡፡
በዚህም መሰረት ቢኤምደብሊውን የመሳሰሉ ግዙፍ የመኪና አምራቾች ተመሳሳይ አገልግሎት ያላቸውን ተሽከርካሪዎች በማቅረብ በግዢው ላይ እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ የተሻሻለውን ሰነድ አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የኩባንያው ባለቤት ኢለን መስክ “መስርያቤቱ ከቴስላ ጋር የ400 ሚሊየን ዋጋ ያላቸው የተሽከርካሪ ግዢ ለመፈጸም ማቀዱን አላውቅም ነበር” ብሏል፡፡
በጆ ባይደን የስልጣን ዘመን ወጥቶ የነበረው የግዢ እቅድ ትራምፕ ስልጣን ከመያዛቸው ከሳምንታት በፊት እንደተሻሻለ በሰነዱ ላይ የተጠቀሰው ቀን አመላክቷል፡፡
የግዢ እቅዱ ለምን እንደተቀየረ የታወቀ ነገር ባይኖርም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔውን ሊሽሩት እንደሚችሉ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡
ቴስላ ሞዴል 3 ፣ ሞዴል s፣ ሞዴል Y እና ሞዴል X ኤስዩቪ እንዲሁም ሴዳን ጥይት የማይበሳቸው የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ያመርታል።
ስፔስኤክስ እና ቴስላን የመሳሰሉ ኩባንያዎች ከመንግስት ጋር ባላቸው ስምምነት እና ኮንትራቶች በአመት በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ገቢ ያገኛሉ፡፡
የሮኬት ኩባንያው ስፔስኤክስ ፕሬዝዳንት ጉዌን ሾትዌል በህዳር ወር ድርጅቱ ከመንግስት ጋር 22 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ኮንትራቶች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡
ኢለን መስክ የመንግስት ተቋማትን ውጤታማነት የሚከታተለው አዲስ ተቋም መሪ ከመሆኑም ተሻግሮ የትራምፕ አስተዳደር ገጽ (ፊት) ሆኗል በሚል ይነሳል፡፡
ቢሊየነሩ ከአዲሱ ፕሬዝዳንት ጋር ባለው የተለየ ቅርበት በአሜሪካ አጠቃላይ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ተሰሚነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት መላበሱንም የተለያዩ የአሜሪካ ሴናተሮች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመሰናበቻ ንግግራቸው መጪው የአሜሪካ መንግስት በባለጸጎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የሚዘወር እንዳይሆን ስጋት እንዳላቸው መናገራቸው ይታወሳል፡፡