የአሜሪካዋ ኦካላሆማ ግዛት የመጸሀፍ ቅዱስ ትምህርት በመንግስት ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ አዘዘች
ግዛቷ ተማሪዎች ከመደበኛው ትምህርት ባለፈ ግብረ ገብ እና ህግ ማክበርን እንዲማሩ መጽሀፍ ቅዱስን ማወቅ አለባቸው ብላለች
በቅርቡ ሌላኛዋ የአሜሪካ ግዛት ሊውዚኒያ አስርቱ ትዕዛዛት በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ እንዲለጠፉ መወሰኗ ይታወሳል
የአሜሪካዋ ኦክላሆማ ግዛት በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመጸሀፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲሰጥ ወስናለች።
ግዛቷ በሁሉም የመማሪያ ክፍል ውስጥ መጸሀፍ ቅዱስ እንዲቀመጥ ያዘዘች ሲሆን ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን ተማሪች መጸሀፍ ቅዱስን እንዲያውቁ አስተማሪዎች እንዲቀጠሩ መመሪያ አውርዳለች።
ውሳኔውን ያሳለፉት የትምህርት ባለሰልጣናት ተማሪዎች ከሰዎች ጋር እንዴት መኖር እንደሚችሉ ፣ አገልጋይነትን ፣ ርህራሄን ፣ መልካምነትን እና ግብረገብነትን እንዲማሩ መጸሀፍ ቅዱስ ወሳኝ መሳርያ ነው ብለዋል።
ባለስልጣናቱ የአሜሪካን ህገ መንግስት ለመቅረጽ መጸሀፍ ቅዱስ የመጀመርያ ምንጭ ነበር ያሉ ሲሆን፤ በተጨማሪም ተማሪዎች ህግን መከተል እና ማክበርን ያውቁ ዘንድ አስርቱን ትእዛዛት እንዲማሩ ወስነዋል።
በግዛቷ የሚገኙ ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከአምስተኛ እስከ 12ተኛ ክፍል በሚገኙ ተማሪዎቻቸው ላይ መመሪያውን በፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደረጉም አዘዋል።
በመንግስት እና በሀይማኖት መካከል ሊኖር የሚገባውን ልዩነት የሚጥስ ነው ያሉ የሲቪል መብት ተሟጋቾች በውሳኔው ላይ ትችት ሰንዝረዋል።
የመብት ተሟጋቾቹ በአሜሪካ ከሚገኙ 50 ግዛቶች በትምህርት ጥራት 49ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝው ኦክላሆማ ከመጸሀፍ ቅዱስ ይልቅ መደበኛውን የትምህርት ስርአት ማሻሻል ላይ ብታተኩር ይሻላል ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም በአሜሪካ ህገ መንግስት የሀይማኖት ነጻነትን እንዲሁም በሀይማት እና በመንግስት መካከል ሊኖር የሚገባውን ልዩነት የሚጠቅሰውን ድንጋጌ በማንሳት ውሳኔ ኢህገ መንግስታዊ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።
የግዛቷ የመምህራን ህብረት በበኩሉ ስነ ምግባር እና ለህግ መገዛትን ማስተማር መጥፎ ባይሆንም ተማሪዎችን ከአንድ ሀይማኖት ጋር ብቻ እንዲተሳሰሩ ማስገደድ ተገቢ አይደለም ብሏል።
በቅርቡ የአሜሪካዋ ሊውዚኒያ በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ አስርቱ ትዕዛዛት እንዲለጠፉ ማዘዟ ይታወሳል።
በዚህ ውሳኔ መሰረት በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ በሚደረግላቸው ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ ከ2025 ጀምሮ በሁሉም የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ አስርቱ ትዕዛዛት የተጻፉባቸው ፖስተሮች እንዲለጠፉ ተወስኗል።
በ1980 ኬንታኪ መሰል ህግ አውጥታ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት የሃይማኖትና መንግስትን መለያየት ይቃረናል በሚል ውድቅ አድርጎት ነበር።