ትራቪስ ኪንግ በክህደትና በሌሎችም ወንጀሎች በይፋ ክስ እንደሚመሰረትበት ተነግሯል
ባለፈው ወር ከደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን ኮሪያ ሸሽቶ የገባው የአሜሪካ ወታደር ትራቪስ ኪንግ በክህደት፣ የልጅ ወሲባዊ ምስሎችን በመጠየቅ እና በመያዝ ክስ እንደሚመሰረትበት ተነግሯል።
ክሱ በወታደሮች ላይ ጥቃት መሰንዘርንም ይጨምራል ተብሏል።
የስለላ ባለሞያ የሆነው ትራቪስ ኪንግ ባለፈው ሀምሌ ወር በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሰሜን ኮሪያ መሻገሩ ይታወሳል።
በመጨረሻም ፒዮንግያንግ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ሳትሰጥ ወታደሩን መልቀቋ ተነግሯል።
ክሶቹ እስካሁን ገና በይፋ ባይገለጹም ስምንት ክሶች መቅረባቸውን ግን ቢቢሲ ሮይተርስን ጠቅሶ ዘግቧል።
የ23 ዓመቱ ወጣት በሀምሌ ወር ወደ ሰሜን ኮሪያ ሸሽቶ በመሄዱ ብቻ በክህደት ክስ ሊታሰር ይችላል ተብሏል።
ወታደሩ ባለፈው ዓመት ከአሜሪካ ጦር ለማምለጥ ያደረገውን ሙከራ ጨምሮ ሰፊ የስነ-ምግባር ጉድለት እንዳለበት ተጠቅሷል።
ትራቨስ ኪንግ ከጥር 2021 ጀምሮ በሰራዊቱ አባል የሆነ እና በደቡብ ኮሪያ ውስጥ ተመድቦ የነበረ ነው።
ኪንግ ወደ ሰሜን ኮሪያ ከመሸሹ ከስምንት ቀናት በፊት በሁለት ሰዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ለሁለት ወራት በእስር ቆይቷልም።
ወታደሩ ወደ ሰሜን ኮሪያ ለምን እንደሸሸ፣ ምን አይነት አቀባበል እንደተደረገለት እና በፒዮንግያንግ ለምን በነጻ እንደተለቀቀ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም።