የአሜሪካ ባለስልጣናት ከታሊባን አመራሮች ጋር ፊትለፊት ሊገናኙ መሆኑን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ
ታሊባን ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላ ከአሜሪካ መንግስት ጋር የሚያደርገው የመጀመሪያው የፊትለፊት ንግግር ይሆናል
የአሜሪካ ባለስልጣናት ዛሬ እና ነገ ከታሊባን ተወካዮች ጋር በኳታር መዲና ዶሃ ይገናኛሉ ተብሏል
የአሜሪካ እና የታሊባን አመራሮች ዛሬ እና ነገ ፊት ለፊት ተገናንተው ሊወያዩ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡
የዋሸንግተን ባለስልጣናት ዛሬ እና ነገ ከታሊባን ተወካዮች ጋር በኳታር መዲና ዶሃ እንደሚገናኙም ነው መስሪያ ቤቱን ጠቅሶ ፍራንስ 24 የዘገበው፡፡ ታሊባን ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ንግግር ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን በአካል የሚደረገው ውይይት ግን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በኳታሩ ውይይት ሁለቱንም ወገኖች ወክለው የሚቀርቡ ባለስልጣናት እነማን እንደሆኑ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አልተናገሩም ተብሏል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ታሊባን የሁሉንም አፍጋናውያን መብት እንዲያከብር እንደሚያሳስቡ ተናግረዋል፡፡ ሴቶችና ህጻናት መብታቸው እንዲከበር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ መንግስት እንዲመሰረት ዋሸንግተን ትፈልጋለች ብሏል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፡፡ የሚመሰረተው መንግስትም የብዙኃን ድጋፍ ሊኖረው እንደሚገባ ነው አሜሪካ ጠይቃለች፡፡
አፍጋናውያን የኢኮኖሚና የሰብዓዊ ቀውስ ስለገጠማቸው ታሊባን የሰብዓዊ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲገቡ ማመቻቸት አለበትም ብላለች፡፡
የአሜሪካ ባለስልጣናት ከታሊባን አመራሮች ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ውይይት አደረጉ ማለት ዋሸንግተን ለቡድኑ ዕውቅና ሰጥታለች ማለት እንዳልሆነም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡ አሜሪካ አሁንም ቅቡልነት ይመጣል ብላ የምታምነው ታሊባን በሚደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እንደሆነ ገልጻለች፡፡ አሜሪካ ዜጎቿን ከካቡል ለማስወጣት ተልዕኮዋን ስትፈጽም ታሊባን ትብብር ማድረጉን መግለጿ ይታወሳል፡፡
አሜሪካ ቀደም ሲል የፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒን መንግስት ስትደግፍ እንደቆየች የሚታወስ ቢሆንም አሁን ደግሞ ካቡልን ከተቆጣጠረው ታሊባን ጋር የፊት ለፊት ውይይት ልታደርግ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡