ታሊባን በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ለማድረግ ጠየቀ
ታሊባን በኒውዮርክ ንግግር ለማድረግ ያቀረበውን ጥያቄ የተመድ ኮሚቴ እንደሚመለከተው ይጠበቃል
ጥያቄውን የሚመለከተው ኮሚቴ ውስጥ አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ ይገኙበታል
አፍጋኒስታንን በመምራት ላይ የሚገኘው ታሊባን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቡ ተገለጸ።
በኒውዮርክ ንግግር ለማድረግ ታሊባን ያቀረበውን ጥያቄ የተመድ ኮሚቴ እንደሚመለከተው ይጠበቃል።
አሁን ላይ ቡድኑ በዶሃ ቢሮው ቃል አቀባይ ያደረገውን ሱሃይል ሻሄንን በተመድ የአፍጋኒስታን አምባሳደር አድርጎ መምረጡን አሶሺየትድ ፕሬስ አስታውቋል።
እንደ ተመድ ቃል አቀባይ ቢሮ ገለጻ ከታሊባን የቀረበውን ንግግር የማድረግ ጥያቄ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ እንደሚመለከተው የተገለጸ ሲሆን በዚህ ኮሚቴ ውስጥ አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ ይገኙበታል።
ተመድ በታሊባን ጥያቄ ላይ ውሳኔ እስከሚያሳልፍ ድረስ ጉህላም ኢዛቻ በተመድ የአፍጋኒስታን አምባሳደር ሆነው እንደሚቀጥሉ ቢቢሲ ዘግቧል።
አምባሳደር ጉህላም ኢዛቻ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የመጨረሻ እለት ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ይሁንና ታሊባን ግን ዲፕሎማቱ አፍጋስታንን ከዚህ በኋላ እንደማይወክሉ ገልጿል።
76ኛው ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በአሜሪካዋ ኒውርክ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የበርካታ ሀገራት መሪዎች እና ተወካች በጉባዔው ላይ ተገኝተው ንግግር እያደረጉ ነው።
በትናትናው እለትም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጀት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመጀመሪያ ንግግራቸውን አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በንግግራቸው ዓለም ላይ የተደቀኑ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ እና ለማሸነፍ ዋሸንግተን ከቀሪው ዓለም ጋር ተባብራ መሥራት እንዳለባት ገልጸዋል። ሀገራቸው በቀጣይ የቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላታም ገልጸዋል።