አሜሪካ በአልቡርሃን ላይ ማዕቀብ ልትጥል ነው
የባይደን አስተዳደር የሱዳን ጦር በንጹሃን ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ፈጽሟል፤ የሲቪል መሰረተልማቶችን አፍርሷል በሚል ይወቅሳል
የአሜሪካ ግምጃ ቤት በቅርቡ በፈጥኖ ደራሽ ሃይል መሪው ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ላይም ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል
አሜሪካ በሱዳን ጦር መሪው አብዱልፈታህ አልቡርሃን ላይ ማዕቀብ ልትጥል ነው።
ሬውተርስ ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን ሶስት ምንጮች ጠቅሶ እንዳስነበበው፥ አልቡርሃን ማዕቀቡ የሚጣልባቸው የሚመሩት ጦር በንጹሃን ላይ ጥቃት ማድረሱና በሲቪል መሰረተልማቶች ላይ ጥቃት ፈጽሟል ተብሎ ስለታመነበት ነው።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ከዘጠኝ ቀናት በፊት በአልቡርሃን ተቀናቃኝ ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ እና ከፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሰባት ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።
በአልቡርሃን ላይ የሚጣለው ማዕቀብም ሁለቱም ተፋላሚ ሃይሎች ለሱዳናውያን ሰቆቃ ተጠያቂ መሆናቸውን በማሳየት ወደ ንግግር እንዲመለሱ ጫና ለመፍጠር መሆኑ ተዘግቧል።
የሱዳን ጦር የአሜሪካ ግምጃ ቤት አሳልፎታል ስለተባለው ማዕቀብ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።
ሱዳንን ለ30 አመት የመሩትን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በ2021 በጋራ በመፈንቅለ መንግስት ያነሱት አልቡርሃን እና ዳጋሎ (ሄሜቲ) ተስማምተው ከሁለት አመት በላይ አልዘለቁም።
በሚያዚያ 2023 የጀመሩት ጦርነት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያንን ህይወት ቀጥፎ ከ14 ሚሊየን በላዩን ከቀያቸው አፈናቅሏል።
የ20 ወሩ ጦርነት ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት ቻድ፣ ግብጽ እና ደቡብ ሱዳን እንዲሰደዱም አድርጓል።
ሁለቱም ተዋጊ ሀይሎች በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በሚከሰሱበት ጦርነት ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለከፍተኛ ርሀብ መጋለጣቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ኤጄንሲዎች ሪፖርት ያመላክታል፡፡
አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ የመሩት የአፍሪካ ህብረት፣ አረብ ኤሜሬትስ እና ሌሎችም ሀገራት በታዛቢነት የተሳተፉበት ተፋላሚዎቹን ለማስማማት የተደረገው ጥረት ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ያሸማገለችው ቱርክ በቅርቡ ጀነራሎቹን ለማደራደር ያቀረበችው ጥያቄ በሱዳን ጦር ተቀባይነት ማግኘቱ ተስፋ ሰጪ ሆኗል።
አሜሪካ በተፋላሚዎቹ ላይ የጣለችው ማዕቀብ አስገድዶ ወደ ድርድር ያመጣቸዋል ወይ የሚለውም በቀጣይ ይታያል።