መጠለያዎቹን በተያዘውና በቀጣዩ ወር ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከአንድ ወር በፊት ስራ መጀመሩ ተነግሯል
በትግራይ ክልል 20 ከተሞች ክረምቱ ከመግባቱ አስቀድሞ ለተፈናቃዮች በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ጊዜያዊ መጠለያዎች እንደሚገነቡ ተገለጸ፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፤ ለመጠለያ ግንባታና ቁሳቁስ ድጋፍ የሚውል የ50 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን፣ ሴቭ ዘችልድረን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መገኘቱን ገልጿል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ሥራ አስፈፃሚና የአስቸኳይ ምግብ ዕርዳታ ኃላፊ አቶ አበበ ገብሬ፤ መጠለያዎቹን በግንቦት እና ሰኔ ወራት ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከአንድ ወር በፊት ስራ መጀመሩን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
እያንዳንዱ መጠለያ ከ15 ሺህ በላይ ዜጎችን እንደሚያስተናግድ የጠቀሱት ኃላፊው፤ እስከ አሁን የመቀሌ መጠለያ በ60 በመቶ ግንባታው እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል።
ተመድ በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ምላሽ የሚሆን 65 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ከሰሞኑ ማስታወቁና ከድጋፉ 40 ሚሊዬን ዶላር ያህሉ ለትግራይ የሚውል ነው መባሉ የሚታወስ ነው፡፡
“በመቀሌ ለክረምት የሚሆኑ ተጨማሪ መጠለያ ጣቢያዎችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው”
ትናንት በክልሉ ጉብኝት ያደረጉት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አብርሀም በላይ (ዶ/ር) ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ተፈናቅለው በመቀሌ ለሚገኙ ዜጎች ለክረምት የሚሆን ጊዜያዊ መጠለያ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚው ተፈናቃዮቹ ያሉባቸው መጠለያዎች የጎበኙ ሲሆን ለተፈናቃዮቹ በሂደት ዘላቂ መፍትሄዎች እንደሚመቻቹ ቃል ገብተዋል፡፡
ዶ/ር አብርሀም “አሁን ያለው መጠለያ በቂ ባይሆንም በአስቸኳይ ሊጠናቀቅ የሚችልባቸውን መንገዶችና አማራጮች እንድመለከት” እድል ሰጥቶኛል ነው ያሉት፡፡
ስራው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ መቀመጡንም ጭምር ነው የተናገሩት፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በቅርቡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መሾማቸው የሚታወስ ነው፡፡